አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በታህሳስ 2024 በቱርክ የተፈረመው የአንካራ ስምምነት እንደሚመራ አስታወቀች። ይህ መግለጫ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በ2024 መጀመሪያ የፈረሙት አወዛጋቢ የመግባቢያ ሰነድ አሁንም በሕግ ላይ እንዳለ ወይም እንደታገደ የሚነሱ ጥያቄዎችን በማቃለል የተሰጠ ነው።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር አሊ መሐመድ ኦማር ለሳዑዲ የዜና ጋዜጣ አሽርቅ አል-አውሳት በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ በሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድና በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መካከል በቱርክ የተደረሰው ስምምነት አዲስ የግንኙነት ማዕቀፍ መፍጠሩን ገልጸዋል።
እንደ ኦማር ገለጻ፣ ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነፃነትና የግዛት ሙሉነት ለማክበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።
ኦማር የ2024ቱ የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ ታግዷል ወይም ተሰርዟል በሚል ክርክር ላይ ብዙ ጊዜ ማጥፋት እንደማያስፈልግ ገልጸው፣ በአንካራ ማዕቀፍ መሠረት ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚደረጉ የንግድ ስምምነቶች መንገድ መከተል እንደምትችል ጠቁመዋል። ሆኖም ማንኛውም ስምምነት በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ሥር መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአንካራ ማዕቀፍ ሥር የቴክኒክ ድርድር በየካቲት 2025 የጀመሩ ሲሆን፣ ቱርክም በሽምግልና ሚናዋ ቀጥላለች። ድርድሩ ኢትዮጵያ የባሕር በር በንግድ ስምምነቶች እንድታገኝና የሶማሊያ የግዛት ሙሉነት እንዲጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመመርመር ያለመ ነው። በዚህ ማዕቀፍ መሠረት የወደብ ኪራይ፣ የንግድ ውሎችና ሌሎች የባሕር ተደራሽነት ስምምነቶች ሊደረጉ ይችላሉ።
የሶማሊያ ባለሥልጣኑ መግለጫ ሞቃዲሾ በኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ላይ ያለውን አቋም በግልጽ የሚያሳይ ሲሆን፣ በሶማሊላንድ በኩል ከሚደረጉ ስምምነቶች ይልቅ በሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ጋር በሚደረግ የንግድ ድርድር ላይ እንደሚያተኩር ጠቁሟል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






