አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | መንግሥት ይፋ አላደረገውም እንጂ አዲስ አበባን ለማውደም በመቶዎች የሚቆጠሩ የድሮን ጥቃቶች ተፈጽመው ነበር። የህወሃት የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች የድሮን ጥቃት እንደሚጀመርና እንደ አየር መንገድ ያሉ የሲቪል ተቋማት ሳይቀር እንደሚመቱ ሲዝቱና ጉዳት እንደደረሰባቸው በድል አድራጊነት አስታውቀዋል። በይፋ ባያስታውቅም የሀገር መከላከያ የአየር ምድብ ሁሉንም ሙከራዎች እንዳከሸፈ አዲስ ሪፖርተር አረጋግጧል።
ሕዝብ በሚበዛባቸው ሞሎች፣ በገበያ ተቋማት፣ በተለያዩ አየር መንገዶች እና ቢሮዎች ላይ ዒላማ ያደረጉ የድሮን ጥቃቶች የተሞከሩ መሆኑን አሜሪካ ዘግይታም ቢሆን ይፋ አድርጋለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙትን ጥቃቶች ከተገንጣይ ቡድኖች እንቅስቃሴ እና ከሽብር ተግባራት ጋር አያይዘው እንዳሉት ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሆነችውን አዲስ አበባን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን አሜሪካ ታውቃለች።
አዲስ አበባን ዒላማ ያደረገውን የድሮን ጥቃት ከሽብርተኝነት ጋር ያያዙት ማርኮ ሩቢዮ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየተዋጉ የሚገኙትን ኃይሎች “ተገንጣይ ቡድን” (separatist) ብለዋቸዋል። በሀገሪቱ ውስጥ ጥቃት የሚፈጽሙ ተገንጣይ ቡድኖች በመኖራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዚህ ጥቃቶች ምላሽ እየሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።
“ማንም ቢሆን ሽብርተኝነትን፣ በዋና ከተማቸው ላይ የተፈጸሙትን የድሮን ጥቃቶች ጨምሮ አይደግፍም” በማለት “ሽብር” ያሉትን ተግባር አውግዘዋል። አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ከእነዚህ “ተገንጣይና የሽብር ተግባር ከሚፈጽሙ ኃይሎች” የሚሰነዘርበትን ፈተና በሚገባ እንደምትረዳም በይፋ አስታውቀዋል።
ሩቢዮ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር በስልክ ከተነጋገሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ህወሃት የከፈተውን ውጊያ ከሽብር ጋር አያይዘው በይፋ ማውገዛቸው፣ በውጭ ሀገር ባለው የህወሃት ሴል እና መሣሪያ ግዢ ላይ የተሰማሩትን እንዳስደነገጠ ለሰዎቹ ቅርብ የሆኑ ወገኖች አመልክተዋል።
በተገንጣይ ቡድኖች እንቅስቃሴ እና በተወሰዱት ምላሾች ምክንያት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበሮች አቅራቢያ የጦር ኃይሎች ክምችት እየጨመረ መሄዱ እንዳሳሰባቸው ያመለከቱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሁለቱም ሀገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ድንበር ማስጠጋታቸው ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ጭምር የሚያካትት ሰፊ ቀጠናዊ ጦርነት ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል።
አሜሪካ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ጥላው የነበረውን አነስተኛ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ያነሳችው ከሁለቱም ወገኖች ጋር በመነጋገር የሰላም አስከባሪነት እና የአደራዳሪነት ሚናዋን ለመወጣት እንደሆነና ይህም ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል።
አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ላለፉት ዓመታት የጠበቀ ግንኙነት ያልነበራት ቢሆንም፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ከተለመደው የተሻለ የሐሳብ ልውውጥ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማድረግ መቻሉን የገለጹት ሩቢዮ፣ በአንጻሩ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር እጅግ የጠበቀና ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከተገንጣይ ኃይሎች የሚገጥማትን ፈተና አሜሪካ በአግባቡ እንደምትረዳ ያመለከቱት ሩቢዮ፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል። አክለውም፣ መንግሥት ለተገንጣይ ቡድኖች ጥቃት የሚሰጠው ምላሽ ጥበብ የተሞላበት እና ሚዛናዊ ሊሆን እንደሚገባው፤ እርምጃው ሌሎች ሀገራትን ጭምር አሳትፎ ወደ አውዳሚ እና የሰፋ ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል። “ዓለም በአሁኑ ሰዓት ሌላ ተጨማሪ ጦርነት አይፈልግም” ብለዋል።
ህወሃት በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት፣ አየር መንገዶች፣ አገልግሎት መስጫዎችና ሕዝብ በብዛት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ በርካታ የድሮን ጥቃቶችን ቢሞክርም፣ የአየር ኃይል ምድቡ እንዳመከናቸው አዲስ ሪፖርተር አረጋግጧል።
ይህንኑ ጥቃት የውጭ መንግሥታትና ዲፕሎማቶች እንዲያውቁት መደረጉን መረጃውን ካጋሩን አካላት ለማረጋገጥ ተችሏል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ጉዳዩን ከሽብር ጋር ያያዙት ድሮኖቹ ከመጡበት ምንጭ ማንነትና የታቀደውን ዕቅድ ከመረዳት አንጻር እንደሆነ እነዚሁ ወገኖች ግልጽ አድርገዋል።
“ህወሃት በመቀሌ በሚገኘው የአሉላ አባነጋ ኤርፖርት ላይ ጥቃት እፈጽማለሁ” በማለት ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም. መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ዜጎች፦ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የልብ ሕመም፣ የኤች አይ ቪ እና መሰል መድኃኒቶች እንዲሁም ብር ወደ ትግራይ የሚጓጓዘው በአውሮፕላን መሆኑን በመጥቀስ “ህወሃት ጸቡ ከማን ጋር ነው?” ብለዋል።
አየር መንገዱ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር ይፋ ያደረገው ህወሃት፣ በኢንሹራንስ ሥጋትና ከደህንነት ችግር ጋር ተያይዞ ወደ መቀሌ የሚደረግ በረራ ቢቋረጥ “ማን ይጎዳል?” ለሚለው ጥያቄ ካለበት ሆኖ ባሰራጨው መግለጫ ይፋ አላደረገም። በረራ ቢቋረጥ የሚጓደሉትን የሕዝብ ፍላጎቶች በምን መልኩ እንደሚያሟላም አላመላከተም።
“ህወሃት ለፌደራል መንግሥትና ለዓለም ‘እባካችሁን አሸባሪ በሉኝ’ በማለት ማመልከቻ እንዳስገባ ይቆጠራል” ያሉ የትግራይ ሰላም ኃይሎች አመራር፣ ሱዳንን ጨምሮ ህወሃት አብሮ የሚሰራው ከሽብርተኛ አካላት ጋር በመሆኑ ማመልከቻው ተቀባይነት ሲያገኝ ጣጣው ይህን ሳያውቁ ሲያግዙት ለነበሩት የሚተርፍ መሆኑ እንደሚያሳዝናቸው አመልክተዋል።
ህወሃት ጦርነቱን በበላይነት ለመጨረስ ታጣቂዎችን ሰብስቦ ጥምረት መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ያከማቸው የመሣሪያ ብዛት ያስደነገጣቸው ዜጎች “ዝግጅታቸው ምን ለማድረግ ነበር?” በማለት ይጠይቃሉ። ድሮንን ጨምሮ በቁጥጥር ሥር የዋለውን መሣሪያ ለመግዛት፣ ለማጓጓዝና መለዋወጫውን ለማስመጣት የወጣው ሀብት ለልማት ቢውል ኖሮ ትግራይን ከፍተኛ ቦታ ያደርሳት እንደነበር በመግለጽ ቁጭታቸውን ያስቀምጣሉ።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






