አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ |የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ለመገኘት አስቀድመው ወደ ሩሲያ ያቀኑት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ “ልዩ አቀባበል ተደረገላቸው” በሚል የቀድሞ ተቃዋሚዎቻቸውና “ጄኖሳይደር” በማለት ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲዘምቱባቸው የነበሩ የህወሃት ደጋፊ ሚዲያዎች አሞካሽተዋቸው ነበር። ዘግየት ብለው ወደ ስብሰባው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሩሲያን መርገጣቸውን ተከትሎ የወጣው ዘገባ ግን ዓለምን ያነጋገረ፣ በአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ትርጉም የተሰጠው፣ በተለይም ፕሬዚዳንት ፑቲን ለሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ ቀይ መብራት ያሳዩበት እንደሆነ ተመልክቷል።
“ሩሲያ በሁለቱ ሀገራት መካከል “አስታራቂ” ለመሆን ብትሞክርም፣ ለኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ከተያዘለት ጊዜ አንድ ዓመት ቀድማ ማድረሷ ለኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ መገለልን ወይም ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን የሚያሳይ ቀይ መብራት ሊሆንባት ይችላል” በማለት ሮይተርስ በዜናው አካቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልን የአየር ላይ የመከላከል እና የማጥቃት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የተነደፈውን ስትራቴጂ ተከትሎ፣ 12 የሩሲያ ሰራሽ ሱ-35 (Su-35 4++ Generation) ተዋጊ ጄቶችን እንዲሁም የአገሪቱን ሰማይ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ 4 የኤስ-400 (S-400 Missile Batteries) የረጅም ርቀት የአየር መከላከያ ስርአቶችን ከሞስኮ መረከባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የዓለም ሚዲያዎች ዜናውን ሲቀባበሉት አስተያየትና ትንቢታቸውን አክለዋል።
ፈራርሶ ዳዋ የበቀለበት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለውጡን ተከትሎ ዳግም ሲወለድ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ቀድሞ ከነበረው አቅሙ በተጨማሪ አሁን የተጨመረለት አቅም የኢትዮጵያን ወታደራዊ አቅም በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ እንደሆነ ተመልክቷል። ኃይልን በጥራት ማሳደጉ ራቅ ላሉት አገራት ቢሆንም፣ የኤርትራን የመከላከያ ስትራቴጂ የሚፈታተን ስለመሆኑ በርካታ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
የኤስ-400 (S-400) መከላከያ ሥርዓት እስከ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ያሉ ተተኳሾችንና ተዋጊ ጄቶችን የማምከን አቅም ስላለው፣ በድንበር አቅራቢያ ቢቀመጥ የኤርትራን አጠቃላይ የአየር እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መጋረድና መቆጣጠር (Anti-Access/Area Denial) እንደሚችል አናሉዱ ዘግቧል። እዛው ሞስኮ ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ በዚህ መጠን ዘመኑ የወለዳቸውን መሳሪያዎችን ስትታጠቅ በዓይናቸው አይተዋል።
አልጃዜራ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጠቀሱት ዘመናዊ ግዢዎች የተፈጸሙት “ጥቃትን ቀድሞ ለማክሸፍ” (Preemptively deter aggression) ነው ማለታቸው፣ኢትዮጲያ የዓሰብን ጉዳይ በኃይል ለመወሰን ወይም ከኤርትራ ሊሰነዝርባት የሚችለውን የመከላከል እርምጃ ቀድሞ ለመግታት የታለመ የጦርነት ዝግጅት አድርጋ እንድትተረጉመው ያደርጋታል ሲል ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኩል ሎኖር የሚችልውን ስጋት በዜና ትንተና ሰርቷል።
በውጭ አገር የሚኖሩ የቀድሞ የአየር ኃይል አብራሪ ለአዲስ ሪፖርተር ሲናገሩ “በዕውነት ዜናውን ማመን ተስኖኛል” ብለዋል። አክለውም ሩሲያ ለበርካታ አገራት ያላደረገችውን ሽያጭ ለኢትዮጵያ መፍቀዷ እንደሚደንቃቸው አስታውቀዋል።
የኤስ-400 (S-400) “የማይታይ ግዙፍ የመከላከያ ጥላ“

የኤስ-400 ሚሳይል መከላከያ ባትሪ ማለት በአንድ አገር ሰማይ ላይ የሚዘረጋ “የማይታይ ግዙፍ የመከላከያ ጥላ“ እንደማለት ነው። ይህ ሲስተም በአንድ መኪና ብቻ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን፣ እርስ በርሳቸው በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የተገናኙ የጭነት መኪናዎች ስብስብ ነው፦
- የመከላከያ “ዓይን” (ራዳር)፦ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የሚመጡ የጠላት ድሮኖችን፣ የጦር አውሮፕላኖችን እና የሚሳይል ጥቃቶችን አስቀድሞ የማየት አቅም አለው።
- የመከላከያ “አንጎል” (እዝ ማእከል)፦ በራዳር የታዩትን የጠላት አውሮፕላኖች ፍጥነትና አቅጣጫ በፍጥነት በማስላት እንዴት መምታት እንዳለበት ይወስናል።
- የመከላከያ “ጡንቻ” (ሚሳይል ማስወንጨፊያ)፦ በትላልቅ ቱቦዎች ውስጥ የተሸከሟቸውን ሚሳይሎች ወደ ሰማይ በመተኮስ፣ የጠላትን አደጋ አየር ላይ ሳለ ያመክናሉ።

የዚህ ዘመናዊ ትጥቅ ዋና ዓላማ የሀገሪቱን ታላላቅ ብሄራዊ ጥቅሞችና መሰረተ ልማቶች ከተደቀነባቸው የውጭ ጥቃት መከላከል ነው።
- የታላቁ የኢትዮጵያ ዓባይ ግድብ ጥበቃ፦ ግድቡ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋስትና በመሆኑ፣ እንደ ግብፅ ያሉ ቀጠናዊ ተቀናቃኞች በተደጋጋሚ ወታደራዊ የሃይል አማራጮችን ሲጠቅሱ ቆይተዋል። ይህ የኤስ-400 ስርአት በግድቡ ዙሪያ ማንም ሊደፍረው የማይችል “የበረራ ክልከላ ቀጠና” (No-Fly Zone) ይፈጥራል።
- የድንበር ደህንነትን ማረጋገጥ፦ ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት መሻከር ማሳየቱን ተከትሎ፣ ይህ ስርአት ማንኛውንም ከድንበር ማዶ የሚመጣን የአየር ስጋት ገና ሳይጠጋ የማክሸፍ አቅም ይሰጣል።
- የቀጠናው ልዕለ–ኃያል መሆን፦ ሱ-35 ጄቶችን ከኤስ-400 መከላከያ ጋር በማቀናጀት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪካ ቀጠና ውስጥ ፍፁም የአየር ላይ የበላይነት ያላት ወታደራዊ ኃያል አገር ያደርጋታል።
ምንም እንኳን ይፋዊው የውል ስምምነት በሚስጥር የተያዘ ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ገበያ ዋጋ መሰረት የወጣው ግምታዊ ወጪ እጅግ ከፍተኛ ነው፦
- የኤስ-400 መከላከያ ዋጋ፦ አንድ የኤስ-400 ሲስተም ወደ 1.25 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሲሆን፣ ለጋሻነት የተገዙት አራቱም ሲስተሞች በአጠቃላይ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያወጣሉ።
- የሱ-35 ጄቶች ዋጋ፦ አንዷ ሱ-35 ጄት ከ85 እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የምታወጣ ሲሆን፣ ለ12ቱ ጄቶች እስከ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል።
- አጠቃላይ ወጪ፦ ይህ ወታደራዊ ማሻሻያ በአጠቃላይ ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንትን ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የብድር ማሻሻያ ውስጥ ባለችበት ወቅት ይህንን ግዥ እንዴት ፈጸመች? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ቢሆንም፣ የሩሲያ መንግስት የረጅም ጊዜ ዝቅተኛ ወለድ ብድር ማመቻቸቱ፣ በምግብ እና ማዕድናት ንግድ ልውውጥ (Barter Trade) መተካቱ እንዲሁም ሩሲያ በምዕራባውያን ማዕቀብ ውስጥ በመሆኗ ለኢትዮጵያ ያደረገችው ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ (Sanctions Discount) ለግዥው መሳካት ዋነኛ መንገዶች መሆናቸውን ወታደራዊ ተንታኞች ይገልጻሉ።
የቀጠናው አገራት ስጋት (ግብፅ እና ኤርትራ)
የኢትዮጵያ አዲስ ወታደራዊ አቋም በካይሮ እና በአስመራ በኩል ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል። በተለይም የግብፅ መከላከያ ኃይል በዓባይ ግድብ ላይ ሊሰነዝር የሚችለውን ማንኛውንም ድንገተኛ የአየር ጥቃት አማራጭ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደረገው ሲሆን፣ ካይሮ ከወታደራዊ ዛቻ ይልቅ ወደ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር ብቻ እንድታዘነብል ያስገድዳታል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






