አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | በኤርትራ ያለውን የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ አገዛዝ ለማስወገድ ራሳቸውን ያደራጁ የብርጌድ ንሓመዱ ግንባር የትጥቅ ትግል መጀመራቸውን እና በውጭ አገራት ሙሉ ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን በተለይ ለአዲስ ሪፖርተር አስታወቁ። “ኢትዮጵያዊ ነን ለሚሉ የኤርትራ ተወላጆች ከጠየቁ “የኢትዮጵያ ፓስፖርት ሊሰጣቸው ይገባል” የሚል ጥያቄም ተነስቷል።
የትግራይን ሕዝብ ከህወሃት ኋላ ቀርና በአንድ አካባቢ የተመሰረት የጭቆና ቀንበር ከሰባበሩት የትግራይ የሰላም ኃይሎች ትምህርት መውሰዳቸውን ያመለከቱት የግንባሩ የአዲስ አበባ አስተባባሪዎች ለዲስ ሪፖርተር እንዳሉት ያደራጁት ሰራዊት ወደ ሃራ መሬት እየወጣ ነው።
ብርጌድ ንሓምዱ የነጻነት ትግል ለማድረግ ጠብመንጃ ማንሳቱን አስመልክቶ የዓለም ዓቀፍ አመራሮቹ ተጠይቀው “ዓለም ዓቀፍ እና አህጉር ዓቀፍ ድጋፍ አለን። የኢሳያስ አገዛዝ በመላው ዓለም የሚታወቅና መወገድ ያለበት በመሆኑ ትግሉ መጀመሩ ካልዘገየ በስተቀር ምንም የሚደበቅ አይደለም ተጀምሯል። እስካሁንም የቆየው መሬት ላይ መሰራት ያለባቸው፣ እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚሰሩ ስራዎች መቅደም ስለነበረባቸው ነበር” ሲሉ የትጥቅ ትግል መጀመሩን አረጋግጠዋል።
ከመንግስት ወገን የተባለው የትጥቅ ትግል ስለመጀመሩ ማረጋገጫ ለማግኘት ሙከራ ቢደረግም አልተሳካም። የሆነ ሆኖ በትግራይ ያሉ እማኞች እንዳሉት የብርጌድ ንሓመዱ ሰራዊት ወደ ሃራ መሬት መግባት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኢሳያስ አገዛዝ የሰለቻቸው የሰራዊት አባላት እየከዱ ሃራ መሬት ያለውን ኃይል እየተቀላቀሉ መሆኑን የጠቀሱት የብርጌድ ንሓመዱ የአዲስ አበባ አስተባባሪ፣ በኢሳያስ ሰራዊት ውስጥ ዘልቀው መግባታቸውን አመልክተዋል።
ባለፈው ሳምንት የብርጌድ ንሓመዱ መሪ ከአዲስ ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኤርትራ ሰራዊት ውስጥ ገብተው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተው ነበር። አሁን ላይ ባለው መረጃ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አገዛዝ 32 የሚሆኑ ከፍተኛ መኮንኖችን ከብርጌድ ንሓመዱ ጋር ግንኙነት አላቹህ በሚል አስሯል።
የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የመጨረሻ ዕቅድ ይፋ ሆነባቸው፤ ከወደቁ ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ይሚሰነዝሩ 16 የሽብር ቡድኖች ማደራጀቱን ያመለከቱት የብርጌድ ንሓመዱ መሪ አቶ በየነ፣ ከኢትዮጲያ ብዙ እንደሚጠብቁ ማመልከታቸው አይዘነጋም።
አቶ በየነ ኤርትራ ከኢሳያስ በኋላ እንዴት እንደምትመራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ባስታወቁ ሳምንት ዕድሜ ውስጥ የብርጌድ ንሓመዱ ወታደሮች የትጥቅ ትግል መጀመራቸው በኤርትራ አገዛዞች በኩል ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩን መረጃ እንዳላቸው የአዲስ አበባ ባልደረቦቻቸው አመልክተዋል።
ኤርትራን ያለምርጫ እየገዙ ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ በኢትዮጵያ ተሸንፈው ከሸሹ ወይም ህይወታቸው ካለፈ የሚተገበር አስራ ስድስት የሽብር ቡድኖችን አስቀድመው ማደረጃታቸው ይፋ መሆኑን መዘገባችንም አይዘነጋም።ይህ “እቅድ ሁለት” የተባለው የኢሳያስ ሌላ አማራጭ በሱዳንና ኤርትራ ድንበር ላይ መሰረቱን ቢያደርግም ሴሉ ሰፊ እንደሆነ ተመልክቷል።
«ደም የተከፈለበት ባርነት» የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ አቶ ረዘነ ሃብተ በተለይ ለአዲስ ሪፖርተር እንዳሉት፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በተሰጣቸው ዕቅድ መሰረት ቢሞቱ ወይም ተሸንፈው ኤርትራን ቢለቁ በራሱ የሚተገበር የሽብር ቡድን ዝግጅት ካደረጉ ዓመታት ተቆጥረዋል።
“ባለማወቅ ላይ የነገሱ” በማለት የሚጠሯቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከኤርትራና የኤርትራ ተወላጆች ጋር የተያያዘ ዕቅድ እንደሌላቸው ያወሱት አቶ ረዘነ፣ “ኢሳያስ የሽብር ቡድን ማደራጀቱን በማወቅ ኢትዮጵያዊያን ሊጠነቀቁ ይገባል። የመንግስት ተቃዋሚ ነን የሚሉ ወገኖችም ከዚህ ክፉ የኢሳያስ ወጥመድ ራሳችሁን ጠብቁ” ብለዋል።
አቶ ረዘነ እንዳሉት ሲጀመር ጀምሮ የአረብ ማንነት ባላቸው አካላት ኢትዮጲያን ለማተራመስና ሰላም ለመንሳት የተሳሳተ አጀንዳ በመያዝ የኤርትራን ህዝብ አሳስቶ የበረሃ ትግል የመሩት ኢሳያስ፣ ያደራጁት ቡድን ስልጠናና ሎጂስቲክ ቀደም ሲል በፈጠሯቸው አገራት የሚሸፈን እንደሆነ ገልጸዋል።
በኤርትራ የአገዛዝ ለውጥ ከተደረገ፣ ኤርትራን እንደ አገር ለመምራት የሚያስችል ሲስተም ስለሌለ፣ የተማረ የሰው ኃይል እና መዋቅር ባለመኖሩ ኢሳያስ ያደራጁት ቡድን የታናናሽ የጦር አበጋዞች መፈንጫ ሊያደርጓት ስለሚችሉ፣ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ዝግጅት ልታደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። የሽብር ዕቅዱም የሚቀዳው ከዚያው በመሆኑ ኢትዮጵያን እንደሚጎዳ በማሰብ መንግስት አስፈቶ እንዲያስብ፣ ኤርትራዊያንም ስሜት ከወለደው እሳቤ በመውጣት ሰክነው ሊያስቡ እንደሚገባ መክረዋል።
አቶ ረዘነ አያይዘውም የኤርትራ ተወላጆች በኢትዮጵያ ስደተኛ ሊባሉ እንደማይገባ አመልክተው “ዜግነት ለሚጠይቁ፣ ዜኘትና የኢትዮጲያ ፓስፖርት ሊሰጣቸው ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል። ሙሉውን በሚከተለው ሊንክ ተጭነው ያድምጡ
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






