አንተ አገርህን ብለህ ስትሟገት፣ በየስርቻው የሚዶልቱትን ስታጋልጥ “ባንዳ፣ ተከፋይ” ይሉሃል። እነሱ፣ አንተን “ባንዳና ተከፋይ” የሚሉህ አገር ከሚያፈርሰው ሻዕቢያ የሚባል እስስት ጉያ ስር ተለጥፈው ኢትዮጵያ ላይ በ”ኢትዮጵያዊ” ስም ሲዘምቱ “አገር ወዳድ” ናቸው። “የአይጥ ምስክር ዲንቢጥ” እንደሚባለው፤ ሲጣሉ ሚስጢራቸውን እስኪዘረግፉ ድረስ “አይበገሬው፣ ምትክ አልባው፣ የጀግና ዳር፣ አይተኬው፣ የቁርጥ ቀን” ወዘተ እንዲሏቸው በተፈለፈሉ ሚዲያዎች የገጽታ ግንባታ ይሰራላቸዋል። እነሱን የሚነኩ ላይ ዘር፣ ቤተሰብ፣ ልጅና ዘመድ ሳይመረጥ የማህበራዊ ሚዲያ ቁርስ፣ ምስና እራት ይደረጋሉ። እንዲሸማቀቁ ይዘመትባቸዋል። ይህ ገዳይንና ሟችን አንድ እኩል የሚያነግሰው የሻዕቢያና ወያኔ “ሽንት” ዛሬም ኢትዮጵያን አፍርሶ በፍርስራሿ ላይ “ከበሮ ሊደልቅ” ቋምጧል። ኢትዮጵያዊያን መጨረሻው ሲደርስ ምሱን ይሰጡታል!!
አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ አቋም — ዛሬ ከሁሉም ጊዜ በበለጠ ኢትዮጵያዊያን የቆቅ ያህል ነቅተን የምናስብበት ጊዜ ላይ ነን። ዛሬ ኢትዮጵያ ጠላቶቿ በገሃድ ካስማዎቿን ሰብረው በፍራሿ ላይ ሊቆሙ የመጨረሻ ርብርብ ላይ እንደሆኑ እያየች ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን አንድ ያላቸው ታላቅ ተቋም “የአገር መከላከያ ሰራዊትን” ዳግም አፍረሰው አገሪቱን የሽፍታና የጎበዝ አለቃ መፈንጪያ አድርገው ሊዛበቱ የሚቅበዘበዙትን እያዩም እየታዘቡም ነው። አይሳካም እንጂ የአሁኑ አያያዝ እንደ አገር ህልውና የሚያሳጣን፣ እንደ ህዝብ የሚበትነን “በህልውና አደጋ” ስም ተቀብቶ የመጣ የህልውናችን ጠንቅ ነው።
የሶማሊያን መንግስት ተባብረው የጣሉ፣ ሶማሊያን ተቧድነው አሁን ድረስ በጎበዝ አለቃ ተቧድነው እያወደሟት ነው። ረሃብ፣ ድርቅ፣ ጦርነት፣ ስደትና የርስ በርስ እልቂት እያወደሟት ያላቸው ሶማሊያ ከፊታችን ትታየናለች። ሶማሊያ መውደሟ ብቻ ሳይሆን ለሽብርና አሸባሪ አቀብለዋት ሁከት የሚቀፈቀፍባት ገሃነም ሆናልች።
የሱዳንን መንግስት ተባብረው የጣሉ ለወራት መተማመን አቅቷቸው ዛሬ ሱዳንን በጦርነት እያወደሟት ነው። በሚሊዮን ህዝብ ጨርሰዋል። ሱዳን እንደ ሶማሊያ ሁሉ ድርቅ፣ ረሃብ፣ ስደት፣ ሽብር፣ ወዘተ የሚጠብሳት፣ ዜጎቿም መሄጃ አጥተው እያየን ነው።
ደቡብ ሱዳንን ነጻ ለማውጣት ተማምለው የተነሱ ነጻ በሆኑ ማግስት መባላት ጀመረው ዛሬ ድረስ እየተጫረሱ ነው። በየመን፣ ሊቢያ ራቅ ሲልም በኢራቅና ወዘተ የታየው እውነታ ይህና ይህ ብቻ ነው። የማይተማመኑ ተማምለው አብረው መንግስት ገልብጠው አገርና ህዝብን ሲኦል መጨመር!!
ኢትዮጵያን ለማፍረስና ወደብ አልባ አድርገው ለማስቀረት የተስማሙት ህወሃትና ሻዕቢያ ለጥቅም የተቧደኑ በመሆናቸው በሚሊዮኖችን የጨረሰ ጦርነት ውስጥ ገብተው ያደረሱት ውድመት የሚዘነጋ አይደለም። በቅርቡ በትግራይ መከላከያ ላይ ክህደት ተፈጽሞ በተጀመረው ጦርነት ሻዕቢያ ትግራይ ገብቶ ያደርሰው ሁሉ ማንም የማይዘነጋው የጠላትነት ጥግ ማሳያ ነው።
ህወሃት ከለውጡ በኋላ ተደጋጋሚ ወረራ በማድረግ አማራና አፋር ክልል ያደረሰው፣ በተመሳሳይ የትግራይ ህዝብና ራስዋ ትግራይ እንዲጎዱ የተጫወተው ሚና እንዲሁ የሚረሳ አይደል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምስኪኖች ማለቃቸውም ተነገሮናል። ያማል። ይዘገንናል። “ግን ይህ ሁሉ ለምን ሆነ?” ብለን ስንጠይቅ ምላሹ የስልጣን ጥማት እና ወነበር እንጂ ሌላ ምላሽ አናገኝም።
ቀደም ባለው የህወሃት የወረራና ዳግም መንግስት ሆኖ አራት ኪሎ ለመግባት ያደረገው ሙከራ ምላሽ ሲሰጠው “ጄኖሳይድ” እየተባለ፣ እሱ ደብረ ብርሃን ሲደርስ “ጀግና ጀግና” እያጫወተ የደረሰውን ጥፋት በሰላም ተዘጋ ሲባል ዳግም እልቂት እየተደገሰ ነው።
“በህልውና አደጋ” ስም ኢትዮጵያን የህልውና ጉሮሮርዋ ላይ ለመቆም በግብጽ እና ሻዕቢያ መሪነት ይፋ የሆነው የማይገባቡ ድርጅቶች እና ተገነጣይ ቡድኖች ጥምረት ኢትዮጵያን ከመበተን ውጭ ምን አጀንዳ እንደሌለው አፋችንን ሞልተን እንናገራለን። ሻዕቢያ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ላይ የሚያራምደውን አቋም ስለምንረዳ፣ በገቢር ስለምናውቅ፣ እንደ እስስት እየተቀያየረ እና የበሉበትን ውጪት ሰባሪ በሆኑ ጀሌዎቹ አማካይነት እምብርታችን ውስጥ ሳይቀር የሚፈጽመውንና የሚያስፈጸመውን ስለምንረዳ “ከሻዕቢያ ደጅ አንከጅልም” የሚሉትን ጀኞች እምነት ለማስታወስ እንወዳለን።
ስንመጣ ዋናው የመቆሚያ አለታችን “ኢትዮጵያችን፣ ብሄራዊ ጥቅማችን” በሚል መርህ እንደሆነ በግልጽ አስታውቀናል። ለማንም፣ ለምንም ሳይሆን “ደመናውን አይተን ለአገር ይጠቅማል” ያልነውን በማስቀደም የበኩላችንን ስንል ቆይተናል። በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ መንግስትንም በተደጋጋሚ አሳስበናል። የመንግስት ሆደ ሰፊነት ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነም ስንጠቁመ ኖረናል። አሁን ያለነበት እና የደረስንበት መጨረሻ አገርን የሚያሳጣ በመሆኑ “የኢትዮጵያ ህዝብ ንቃ” ለማለት ለማለት እንወዳለን።
ተገንጣዮች፣ ባንዶች፣ አገር ሻጮችና በፖለቲካ ግልሙትናቸው የሚታወቁ ተሰባስበው ኢትዮጵያን ወደ መላክም ዘመን ያመጣሉ ብለን አናምን። ምግባራቸው በገሃድ የሚታወቅ በመሆኑ አብዝተን እንቃወማቸዋለን። ህዝብ እርስ በርስ እንዲባላ አዋጅ የሚያሰሙ፣ ሌት ተቀን የሚተጉ “ጋዜጠኛ ተብዬዎችን” እየተጠቀሙ የብረሃን አማልክት ለመምሰል የሚክለፍለፉ እልቂት ደጋሾች ኢትዮጵያን ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስበሉ አብረዋልና ዝም አንልም።
አገር አልባ የሆኑ የጠቀስናቸውን አገራት ዓየነት ሆነ በስነ ልቦናና በቁጭት ተሰብረን ለመኖር ስለማንሻ የህንን የትርምስና አገርን ወደ ፍርስራሽነት ለመቀየር የሚወራጭ ኃይል መቃወም የሁሉም አግወር ወዳድ ህዝብ ድርሻ በመሆኑ ይህን ጥሪ እናሰማለን። ሻዕቢያ ድሮ ጉያችን ስር ሆኖ አብሮን እድርና እቁብ እየጠጣ በጎረቤቶቻችን፣ በአብሮ አደጎቻችን፣ በፍቅር ባለደረቦቻችን፣ በዘመዶቻች ወዘተ የፈጸመውን ዛሬ እንዲፈጽም መፈቀድ የለበትም እንላለን። ጦርነቱ ድንበር ላይ ብቻ ስላልሆነ እየንዳንዱ ዜጋ ከርሳም የቀበሌና ወረዳ አመራር ጨምሮ አገሩ ተገቶ መጠበቅ አለበት እንላለን። ሁሉም ዜና በያለበት ሰላይ መሆን ግዴታው ነው።
“ሻዕቢያ ጉያ የሚደረግ ማናቸውን ስምምነት አፍራሽ ነው” በሚል ገና በማለዳው እንዳስረዱን አባቶች፣ አሁን በ”ህልውና” ካባ የሸፍኖ የመጣው የሻዕቢያ ኃይል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስጋት በመሆኑ እንደ አገር አንድ ላይ መቆም አማራጭ ሳይሂኦን የግዴታዎች ሁሉ ግዴታ ነው። ዛሬ አብሮ ከመሆን ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ስንል የተበተኑትን በመመለከት ብቻ ሳይሆን፣ የተሰባሰቡት ሁሉ አጀንዳቸው “መበተን” በመሆኑና በጓዳ ይህን ስምምነት እንዳደረጉ ስለነገሩን ነው።
“ኢትዮጵያ ሶስት ቦታ ትከፈላለች” በማለት ህወሃት በወኪሉ አማካይነት በገሃድ ነገሮናል። እናም ጥያቄው በመበተን ወይስ አንድ መሆን? የሚለው ነው። ሊበትኑን ሲተጉ የኖሩ እባቦች በትነውን ሲሳለቁበን ማየት ወይስ እነሱን አፍርሶ አንድነት ማስከበ? የቱ ይቀድማል?
ህወሃት የብሄርና የልዩነት መርዝ ሲረጭብን ኖሮ ዛሬ ድጋሚ “የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሰበኝ” ብሎ በራሱ የትርምስ ሚዲያ “አስተባብሬ ከሻዕቢያ ጋር ልደርስላቹህ ነው” እያለ ነው። “ጅብ በማያውቁት አገር” እንዲሉ ወያኔን አምነን ደጃችንን እንድንከፍት የጠፈጠፋቸውን ሰብስቦ እየደነሰ ነው። ይህ የትርምስና የዕልቂት ማሽን የሆነ ድርጅት የተነከረበት የደም አበላ መቆሚያ የለውምና ዳግም ሊያጫርሰን በክፋት ልሳኖቹ ታጅቦ የጀመረውን የጥፋት ዝግጅት የአገር መከላከያ ባያመክነው ኖሮ ዛሬ እንደ አገውር የለንም ነበር። ከሰማዩ ተአምር በተጨመሪ ከሰማይ በታች ኢትዮጵያን ወጥሮ ከጠላት የጠበቃትና እየሞተላት ያለው የአገር መከላከያን መደገፍ የዛሬው ወቅታዊ ጥሪ ነው። ከዚህ ውጭ ያለው የጠላት አሳብ ከተሳካ ለመቆጨት እንኳን ጊዜ የለም። ዋ!ዋ! የኢትዮጵያ ህዝቦች በባህልና በቋንቋ ቢለያዩም፣ ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅርና በአስቸጋሪ ጊዜያት የሚመርጡት አንድነት ሀገርን አፅንቶ ያቆየ ታላቅ እሴት ነው። ይህንን እሴት ጠብቀን ከመበታተን እናምልጥ!!
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






