የአውሮፓ ህብረት ተወካዩ ኤርትራና ህወሓት የአፍሪቃ ቀንድ ሰላም እየፈተኑ መሆኑን አስታወቁ፤

Date:

አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | በአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካና የጸጥታ ሁኔታ እየተወሳሰበ በመጣበት ወቅት፣ በኤርትራ አገዛዝ እና በህወሓት አካሄድ ላይ የተነሱ ከባድ የጂኦፖለቲካ ጥያቄዎች የቀጣናውን የወደፊት ሰላምና መረጋጋት እንደገና በትኩረት እንዲታይ አድርገዋል። የቀድሞው የአውሮፓ ሕብረት ልዩ ተወካይ ሰለ አፍሪቃ ቀንድ አሌክሳንደር ሮንዶስ ከዴቪድ ኸርስት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ላይ መመለሷን የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የቀጠናው ሰላምና የአውሮፓም ሆነ ሌሎች አገራት ፍላጎት መሆኑን አንስተዋል።

The fight for the Red Sea, Sudan and the Nile) በሚል ርዕስ ባደረጉት ከታዋቂው David Hearst Podcast ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አሌክሳንደር ሮንዶስ በቀይ ባሕር፣ በሱዳን፣ በናይል ወንዝና በኢትዮጵያ–ኤርትራ ግንኙነት መካከል ያለውን የተሳሰረ የክልሉ የፖለቲካና የደኅንነት ጉዳይ በስፋት ሲያብራሩ ነው ይህንን ያሉት።

3.83 ተከታይ ያለው The David Hearst Podcast ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የቀድሞው የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ተወካይ አምባሳደር አሌክሳንደር ሮንዶስ፣ የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጥያቄ ከሀገራዊ ጥቅም በላይ ከቀጣናው የኢኮኖሚ ውህደት፣ ከዓለም ንግድ ደኅንነትና ከዘላቂ ሰላም ጋር የተያያዘ መሆኑን አስምረውበታል።

ሮንዶስ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እየተዳከመ መምጣቱንና በአዲስ አበባ፣ በአስመራና በትግራይ መካከል ያለው የፖለቲካና የወታደራዊ ስሌት የቀጣናውን ስጋት እንዴት እያባባሰ እንደሚገኝ አንስተዋል። የትግራይንና የሱዳንን ቀውሶች ከቀይ ባሕርና ከቀጣናዊ የኃይል ሚዛን ሽኩቻ ጋር ነጥሎ ማየት ቸግሩን ለመረዳት እንዳይቻል እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

በቃለ ምልልሱ ለመረዳት እንደተቻለው የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት፣ ኤርትራ ለቀይ ባሕር ዳርቻዋና ለዓሰብ ወደብ ያላት ስትራቴጂያዊ ግንዛቤ፣ እንዲሁም የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ተነጣጥሎ የሚታይ እንዳልሆነ ነው። ይህም የቀይ ባሕር ጉዳይ የአንድ ሀገር ወደብ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ ከቀጣናዊ ሰላም፣ ከኢኮኖሚያዊ ትስስርና ከደኅንነት ስርዓት ጋር የተያያዘ ሰፊ ጉዳይ ስለመሆኑ ያመላክታል።

የሮንዶስ ትንታኔ የሚያነሳው ዋና ጥያቄ ይህ ነው፤ በኤርትራና በህወሓት ዙሪያ ያሉ የፖለቲካና የወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የቀጣናውን ሰላም ወደ አዲስ ቀውስ እየገፉት ነውን? የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄስ በግጭት ሳይሆን በሰላማዊ ድርድርና በቀጣናዊ ትብብር እንዴት ሊፈታ ይችላል? እነዚህንና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከተው ውይይት ለቀጣናው የወደፊት አቅጣጫ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች እና መረጃዎችን ያነሳል።

የዴቪድ ኸርስት ፖድካስት በዓለም አቀፍ ፖለቲካ፣ በጂኦፖለቲካዊ ለውጦችና በቀጣናዊ የኃይል ሚዛን ላይ ጥልቅ ውይይቶችን የሚያቀርብ የዲጂታል ሚዲያ መድረክ ነው። ፖድካስቱን የሚያቀርቡት የቀድሞው የጋርዲያን የፖለቲካ ጉዳዮች ዋና ጸሐፊና፣ የሚድል ኢስት አይ (Middle East Eye) መሥራችና ዋና አዘጋጅ ዴቪድ ኸርስት ናቸው። ኸርስት በዓለም አቀፍ ጋዜጠኝነት ረጅም ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ በቢቢሲ፣ በአልጀዚራና በሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይም በዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ተንታኝነት ከመሆኑና 

የቀጣናውን እውነታ ከውስጥ አዋቂ ዲፕሎማት አንደበት

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተደራሽነትና የቀጣናዊ ውህደት ጥያቄ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ውይይቶች ውስጥ እየተሰጠው ያለው ትኩረት ከቀድሞ የተለየ ነው። የቀድሞው የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አምባሳደር አሌክሳንደር ሮንዶስ በዴቪድ ኸርስት ያነሷቸው ሐሳቦች ይህንኑ ጉዳይ ከተናጠል የሀገራዊ ፍላጎት አንጻር ብቻ ሳይሆን፣ ከሰፊው የቀጣናዊ መረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ደኅንነት አንጻር መመልከት እንደሚገባ ማመላከታቸው ይህንኑ እውነት የሚያረጋግጥ ሃቅ ነው።

ሮንዶስ በ2012 እስከ 2021 ድረስ የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ተወካይ ሆነው ያገለገሉና በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በሌሎች የቀጣናው ሀገራት ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ የዲፕሎማሲ ልምድ ያካበቱ ሰው ናቸው። ስለዚህ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ከተራ የፖለቲካ አስተያየት በላይ የቀጣናውን እውነታዎች በዲፕሎማሲያዊና በስትራቴጂያዊ አመለካከት የሚቃኝ ነውና ዝም ብሎ የሚሰጥ የተራ ሰው እይታ ወይም አስተያየት ተብሎ አይወሰደም። ምን አልባትም የአውሮፓ አቋምም ቢባል ማጋነን ላይባል ይችላል። 

በተለይም ኢትዮጵያን ከባሕር ተደራሽነት ውጭ በማድረግ የቀጣናውን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ እንደማይቻል የሚያሳየው የሮዶስ አስተያየት ከላይ የተነሳውን አሳብ የሚያጸና ነው። እንደ እሳቸው አባባል የባሕር በር ጥያቄው የኢትዮጵያ ብቻ የፖለቲካ አጀንዳ ሳይሆን፣ የአፍሪቃ ቀንድ የወደፊት የኢኮኖሚና የጸጥታ ሥርዓት አካል ነው።

“ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትፈልገው ለቀጣናዊ የበላይነት ሳይሆን፣ ለኢኮኖሚያዊ ህልውና፣ ለብሔራዊ ክብርና ለጋራ ብልጽግና ነው”

ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ በዓለም ላይ ከባሕር ወደብ ቀጥተኛ ተደራሽነት የሌላት በሕዝብ ብዛት ትልቋ ሀገር መሆኗ ከቀጣናዊ ጂኦፖለቲካዊ እውነታዎች አንዱ ነው። ይህ ሁኔታ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለዓለም አቀፍ ንግድ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠሩም በላይ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

በዴቪድ ኸርስት ፖድካስት ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የቀድሞው የአውሮፓ ሕብረት ተወካይ አምባሳደር አሌክሳንደር ሮንዶስ ያነሷቸው ሐሳቦች፣ የቀንድ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ዕጣ ፈንታ ከተናጠል ፖለቲካዊ አቀራረቦች በላይ በጂኦግራፊ፣ በኢኮኖሚና በታሪካዊ ትስስር እንደሚወሰን ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተደራሽነት፣ የናይል ውሃ ፍትሐዊ አጠቃቀምና የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ውህደት ጥያቄዎች እንደ የበላይነት ፍላጎት ወይም የጎረቤት ሀገራትን የማስፈራራት አጀንዳ መታየት የለባቸውም። እነዚህ ጉዳዮች ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ህልውና፣ ከብሔራዊ ክብርና ከረጅም ጊዜ የቀጣናዊ መረጋጋት ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ጥያቄዎች ናቸው።

የባሕር በር ጥያቄ፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ አስፈላጊነት

የሱዳን ግጭት፣ በቀጣናው ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ተቃርኖዎችና በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚታዩ የጸጥታ ስጋቶችን እያንዳንዳቸውን ለያይቶ መመልከት የቀጣናውን እውነተኛ ሁኔታ ለመረዳት አያስችልም። የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት በጂኦግራፊ፣ በታሪክ፣ በሕዝብ እንቅስቃሴና በኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት በጥልቅ የተሳሰሩ ናቸው።

ኢትዮጵያ እንደ ቀላል ፖለቲካዊ ምኞት ሳይሆን፣ እንደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ፍላጎት ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር በር ተደራሽነትን ትፈልጋለች። በተለይም እንደ አሰብ ያሉ ወደቦችን በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በጋራ ስምምነት ለንግድ ሥራ የማግኘት ዕድል ለኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አለው።

እያደገ ያለው የሕዝብ ብዛት፣ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያና የንግድ ፍላጎት በአንድ ዋና የወደብ መስመር ላይ በመመርኮዝ ብቻ ሊቀጥል አይችልም። የባሕር በር አማራጮች መስፋፋት የማጓጓዣ ወጪን ይቀንሳል፣ የንግድ ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል፣ አዳዲስ የትራንስፖርትና የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችንም ያበረታታል። ይህ ጥያቄ በጋራ ጥቅምና በሕጋዊ ስምምነት ላይ ከተመሠረተ፣ ለጎረቤት ሀገራትም የንግድ፣ የሥራ ዕድልና የመሠረተ ልማት ጥቅሞችን የሚያመጣ የጋራ ዕድል ሊሆን ይችላል።

የናይል ውሃ፡ ከታሪካዊ ተቃርኖ ወደ የጋራ ብልጽግና

የኢትዮጵያ የቀጣናዊ ትብብር ራዕይ በቀይ ባሕር ብቻ አይገደብም። የናይል ወንዝ ውሃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምም የዚሁ ስትራቴጂያዊ አቀራረብ አካል ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) የኢትዮጵያ የራስን አቅም በመጠቀም የልማት ፕሮጀክቶችን የማሳካት ቁርጠኝነት ምልክት ነው። ግድቡ የንጹህና ታዳሽ ኃይል ምንጭ በመሆን ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ ለሱዳን፣ ለግብፅና ለሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የኃይል ትብብር ዕድል ሊፈጥር ይችላል።

የናይል ውሃ ጉዳይ በታሪካዊ ውዝግብና በአንድ ወገን የበላይነት ፍላጎት ውስጥ መታሰር የለበትም። የተፋሰሱ ሀገራት በፍትሐዊ አጠቃቀም፣ በትብብርና በጋራ ጥቅም መርሆዎች ላይ ተመሥርተው የሚሠሩበት ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል።

በተለይም በሱዳን የሚፈጠር ዘላቂ መረጋጋት፣ በኃይል ልውውጥ፣ በግብርናና በንግድ ትብብር ላይ የተመሠረተ የቀጣናዊ ትስስር እንዲጠናከር ዕድል ይፈጥራል። በዚህ መንገድ ናይል የግጭት ምንጭ ከመሆን ወደ የጋራ ልማትና የኃይል ደኅንነት መሠረትነት ሊሸጋገር ይችላል።

ቀይ ባሕርና ባብ ኤል መንደብ፡ የቀጣናው ሀገራት የጋራ የጸጥታ ኃላፊነት

የባብ ኤል መንደብ ሰርጥና ሰፊው የቀይ ባሕር አካባቢ እየተጋረጡ ያሉ የጸጥታ ስጋቶች ሌላው የቀጣናው ዋና ፈተና ናቸው። የዓለም ንግድ ዋና መስመር የሆነው ይህ አካባቢ በውጭ ኃይሎች የፉክክርና የውክልና ግጭቶች መድረክ ሆኖ መቀጠል የለበትም።

ለረጅም ጊዜ የውጭ ኃይሎች ቀጣናውን በስትራቴጂያዊ ሀብቶች፣ በንግድ መሠረተ ልማቶችና በወታደራዊ መቀመጫዎች ፉክክር መነጽር ሲመለከቱት ቆይተዋል። ነገር ግን የቀጣናውን ሕዝብ፣ የኢኮኖሚ ፍላጎትና የረጅም ጊዜ መረጋጋት የማያካትት የጸጥታ አቀራረብ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም።

በዚህ ረገድ ለቀጣናው የሚያስፈልገው በአካባቢው ሀገራት የጋራ ፈቃድና ተሳትፎ የሚመራ የባሕር ደኅንነት ሥርዓት ነው። እንደ አውሮፓው የደኅንነትና ትብብር ድርጅት (OSCE) መርሆዎች በተመሳሳይ፣ የባሕር ዳርቻ ሀገራትና ከባሕር የተለዩ የቀጣናው ሀገራት በእኩልነት የሚሳተፉበት የጋራ የጸጥታ ማዕቀፍ መፍጠር ይገባል።

የቀጣናው የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ ትብብር ይወሰናል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የቀይ ባሕር ቀጣና መረጋጋት ተቃራኒ ግቦች አይደሉም። ኢትዮጵያን ከባሕር ተደራሽነት በመነጠል ወይም ቀይ ባሕርን የጥቂት ሀገራት ብቻ የተለየ የጥቅም ክልል አድርጎ በመመልከት ዘላቂ ሰላም ማምጣት አይቻልም።

የቀጣናው የወደፊት መረጋጋት በአራት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ይመሠረታል። እነሱም ለኢትዮጵያ ፍትሐዊና ዘላቂ የባሕር ተደራሽነት፣ የጋራ የውሃ ሀብቶችን በፍትሐዊነት ማስተዳደር፣ የቀጣናዊ ንግድና መሠረተ ልማት ትስስርን ማስፋፋት እንዲሁም የዓለም ንግድ መስመሮችን በጋራ መጠበቅ ናቸው። ኢትዮጵያ እንደ ቀጣናው ትልቅ የሕዝብ፣ የገበያና የኢኮኖሚ ኃይል ያላት ሀገር በዚህ የትብብር ሥርዓት ውስጥ ተገቢውን ሚና ልትጫወት ይገባል።

የቀይ ባሕር ወደፊት ዕጣ ፈንታ በግጭት፣ በተናጠል የበላይነት ፍላጎትና በውጭ ኃይሎች ፉክክር ሳይሆን፣ በሕጋዊ ስምምነት፣ በጋራ ጥቅምና በቀጣናዊ ውህደት መወሰን አለበት።ኢትዮጵያ የባሕር በር መፈለግዋ የብቻዋ ጥያቄ አይደለም፤ በጋራ ትስስር የሚገነባው የቀጣናው የወደፊት ብልጽግና መሠረት ነው። የአውሮፓ አማካሪው ማሳረጊያም ይህ ነው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related