አዲስ ሪፖርተር አዲስ ዜና — ከሰሞኑ ከተካሄዱት የድሮን ጥቃቶች ሁሉ የከበደ እንደሆነ ተሰምቷል። ጥቃቱ ከአስራ ሰባት ጊዜ በላይ እንደተካሄደ ተመልክቷል። እማኞች እንዳሉት ከሆነ ጥቃት ከተሰነዘረባቸው በርካታ የተመረጡ ቦታዎች መካከል አራተኛው ላይ የደረሰው ጉዳት ከሁሉም ይልቃል። በድምሩ አምስት ሺህ ታጣቂዎች እጅ ሰጥተዋል። የትግራይ ሰላም ኃይሎች አመራር መረጃ ሰጥተዋል።
ሰሞኑን ከህወሓት፣ ከአካባቢው ምስክሮች፣ እንዲሁም ከቀድሞ የራያ አላማጣ አስተዳደሮች በተገኘ መረጃ መሰረት ከአዲስ መንግስት ምስረታ በፊት ጦርነት ለመጀመር እና ይዞታን በማስፋት ለድርድር አስገዳጅ ሁኔታ ለመፍጠር ዕቅድ መኖሩን ዘግበን እንደነበር ይታወሳል።
በዚሁ ዕቅድ መሰረት እና በምዕራብ ግንባር በደረሰበት ጉዳት ህወሓት በራያ ቆቦና በአፋር አቅጣጫ ጦርነት ለመክፈት አቅዶ የሰው ኃይል እና መሳሪያ ሲያጓጉዝ እንደነበር ይታወሳል። ይህንኑ ተከትሎ የሰባት ድርጅቶች አዲስ ህብረት ይፋ ሆኗል።
“የህልውና ስጋት አሰባሰባቸው” የተባሉት ነጻ አውጪ ድርጅቶችና ግንባሮች መንግስትን አስወግደው የሽግግር መንግስት እንደሚያቋቁሙ ባስታወቁ ማግስት ጥቃት የተሰነዘረባቸው ቦታዎች፦
- ህወሓቶች በተለምዶ «ዝኽረ መለስ» ብለው የሚጠሩት የሓው ጃኖ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በፕሪፓራቶሪ (ንጉሥ ቸኮለ ትምህርት ቤት)፣ ቲቪቲ (TVT) ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት፣
- አበበ ዱቄት ፋብሪካ፣ ራያ ግራንድ ሪዞርት አቅራቢያ፣ እድገት ፋና ትምህርት ቤት፣ ባላ መስመር መምህራን ሰፈር አቅራቢያ፣ በጀሃን፣ ቅልሻ፣ ጋንዳጓሮ፣ ፋጫ፣ ራርሄ፣ ጣፌ፣ ጥሙጋ እና ዋጃ፣
- እንዲሁም በዛታ፣ በመረዋ፣ በጀመዶ እና በራያ ዓዘቦ አካባቢ ካራ ዓዲሻዎ ይጠቀሳሉ።
የራያ ዘብ አባላት በሰጡት መረጃ መሰረት ህወሓት ከፋኖ ኃይሎች ጋር በመሆን ጥቃት ለመሰንዘር በገባባዘው ኪስ አካባቢዎች፣ እንዲሁም መሳሪያ በሸሸገባቸው ስርቻዎች ሳይቀር የድሮን ጥቃት ተካሂዷል። በስም ያልተጠቀሱ ታጣቂዎቹ በሰፈሩባቸው አካባቢዎች በደረሰው ጥቃት የተበተኑ፣ የሸሹ፣ የቆሰሉና ህይወታቸው ያለፈ በርካታ በመሆናቸው ምክንያት ሙሉ መረጃ ማግኘት እንደማይቻል ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት የአየር መከላከያ ኃይል “የተሳካ” ጥቃት ከፈጸመባቸው ቦታዎች በሙሉ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዶ የተገኘው ፋጣ ወይም ጀሃን የሚባለው እና ከአላማጣ ወደ መሆኒ መግቢያ ላይ የሚገኘው ትምህርት ቤት እንደሆነ ተመልክቷል።
ትምህርት ቤቱ ላለፉት አራት ቀናት ከባድ መሳሪያና ተተኳሽ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ተጨናንቆ እንደነበር የገለጹ የዓይን ምስክሮች፣ በዚሁ ትምህርት ቤት በተከማቸው ተተኳሽና ከባድ መሳሪያ ላይ የደረሰው ውድመት ከሁሉም የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለአዲስ ሪፖርተር የደረሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ተከታታይነት ያለው ፍንዳታ እና ተቀጣጣይ ድምጽ ይሰማ ነበር።
የህወሓት ታጣቂዎች በሚከማቹበትና መሳሪያ በሚከዘንባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች በድሮን ጥቃት ስጋት እና ፍርሃት ውስጥ እንደሆኑ፣ የህወሓት ታጣቂዎችም «ቪዲዮና ፎቶ ይቀረጻል» በሚል ስጋት ነዋሪዎችን ወደ ስፍራው እንደማያስጠጓቸው ገልጸዋል። ጥቃቱ ከተከናወነ በኋላ ጩኸት፣ ሩጫ፣ እና መተራመስ እንደነበርና የሆስፒታል ደጆችም ተጨናንቀው እንደነበር እማኞች ገልጸዋል። አልፎ አልፎም መድፍ መተኮስ ጀምረው ነበር።
መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማርፈጃው የተካሄደው የድሮን ጥቃት በአርሚ 26 የ261ኛ ኮር አባላት ላይ የደረሰውን ጉዳት በከፍተኛነቱ ተመዝግቧል። ለህወሓት ወታደራዊ ክፍል ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንዳሉት፣ የደረሰው ሰብአዊ ጉዳት በዳታ ተደግፎ አይገለጽ እንጂ ህወሓትን ክፉኛ አስደንግጧል።
የአርሚ 26 ታጣቂዎች አስተባባሪ አላማጣ ከተማ ለሚገኘው የአርሚ 26 የ262ኛ ኮር አዛዥ ወዲ ወሰን የሰጡትን መመሪያ ጠቅሰው ዜናውን ያጋሩን እንዳሉት፣ ወዲ ወሰን በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ከባድ ቁስለኛ ታጣቂዎችን መሆኒ ከተማ ወደሚገኘው የግንባሩ ህክምና ማዕከል በፍጥነት ማድረስ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የመንግስት ኃይል በግላጭ/በእግረኛ ደረጃ በየትኛውም ግንባር የፊት ውጊያ ገጥሞ እንደማያውቅ ያስታወቁት ምንጮች፣ ውጊያው የቴክኖሎጂ ውጊያ መሆኑ ለህወሓት ኃይሎች ግራ ሆኖባቸዋል።
ህወሓት “በጦርነት አሸንፌ፣ በብልጽግና መቃብር ላይ ስልጣን እይዛለሁ” በማለት በይፋ ካወጀበት ጊዜ ጀምሮ፣ ኃይሉን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ያስጠጋ ቢሆንም፣ በተደጋጋሚ በደረሰበት ያልጠበቀው የድሮን እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት ቀድሞም የመዋጋት ፍላጎት የላቸውም የተባሉት ተዋጊዎቹ ግራ መጋባታቸውን የጦር አዛዦች መናገራቸውን የትግራይ ሰላም ኃይሎች አመራር ለአዲስ ሪፖርተር ገልጸዋል።
እኚሁ አመራር እንደገለጹት፤ በመከላከያ ሰራዊት እጅግ የተቀናጀ እና በጥናት ላይ የተመሰረተ የአየር ጥቃት “ወገናችን የሆኑ” በርካታ ታጣቂዎች እና የጦር መሳሪያዎች ተደምስሰዋል። የበርካታ አርሚዎች የእዝ ሰንሰለታቸው ተበጥሷል። አመራሩም ለራሱ ደህንነት በመስጋቱ የተበታተነውን ታጣቂ ማሰባሰብና ማቀናጀት ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል።
“ወትሮውንም በግድ ታፍሶ የማይመለከተውና ዓላማ በሌለው ጦርነት እንዲማገድ የተፈረደበት ነገር ግን አጋጣሚውን ሲጠባበቅ የነበረው ታጣቂ ወደ መከላከያ ሰራዊትና የሰላም ኃይሉ ለመቀላቀል ሰርግ እና ምላሽ ሆኖለታል። ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ ከህወሓት የከዳው ታጣቂ ብዛት ከአምስት ሺህ በላይ መድረሱን እናውቃለን፤ ይህም በአመራሩ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤና እርስ በእርስ መጠራጠር ፈጥሯል። በዚሁ ከቀጠለ ቡድኑ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መፍረሱ አይቀሬ ነው” በማለት ራሳቸውን እያዘጋጁ መሆናቸውን አመራሩ አመልክተዋል። አክለውም ትብብር ፈጥረው ከህወሓት ጋር ለመሰለፍ የተስማሙት አካላት ወደ መከፋፈል ገብተዋል።
በዛሬው እለት በአላማጣ ስለተወሰደው እርምጃ እና የጉዳት መጠን መንግስትም ሆነ የአገር መከላከያ በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም። ከህወሓት በኩልም የተባለ ነገር የለም። ህወሓት ቆየት ብሎ ሌላ ጊዜ እንደሚያደርገው “ሰላማዊ ሰዎች እና መሰረተ ልማት መጎዳታቸውን ሪፖርት ያደርጋል” ብለን እንጠብቃለን ሲሉ የትግራይ ሰላም ኃይሎች አመራር ተናግረዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






