በተሳሳተ ትርክት ላይ የተገነባ ፖለቲካና ወታደራዊ ስሌት መጨረሻው ሁልጊዜም ውድቀት ነው። ተሳሳተ ትርክት ማለት ያልነበረን ጀግንነት እንደነበረ፣ ያልተገኘን ድል እንደተገኘ፣ እንዲሁም አቅምን ከእውነታው በላይ አጋንኖ በማቅረብ ሕዝብን በቅዠት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የማድረግ ሂደት ነው።
የዚህ ዓይነቱ ትርክት ትልቁ አደጋ መሪዎችንም ሆነ ተከታዮችን እውነታውን እንዳያዩ ማሳወሩ ነው። አንድ ቡድን ወይም ድርጅት ራሱ የፈጠረውን የውሸት ፕሮፓጋንዳ መልሶ ራሱ ማመን ሲጀምር፣ የራሱን አቅም በትክክል መመዘን ይሳነዋል፤ ሌሎችንም ይንቃል። ይህ ደግሞ በተሳሳተ ስሌት ወደ ማይወጡት ጦርነትና ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ይገፋፋቸዋል። ክህወሃት ሰፈር በተደጋጋሚ የታየው እንዲህ ያለው ግትር አካሄድ ነው።
በተጨማሪም፣ ተሳሳተ ትርክት በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ የሚያደርሰው በደል እጅግ ከባድ ነው። “የማንሸነፍ ነን”፣ “አመራሮቻችን ልዩ ችሎታ አላቸው” በሚል የውሸት ቅስቀሳ የተሞላው ወጣት፣ ለሌለ ጀግንነትና ለከንቱ ፕሮፓጋንዳ ሲል ሕይወቱን እንዲገብር ይደረጋል። በዚሁ መነሻ “ጦርነት ባህሉ” እየተባለ የተማገደው የትግራይ ወጣት ቁጥሩን ቤቱ ይወቀው።
የሃሰተኛ ትርክት ሰላባዎች ጩኸት
የሰሞኑ የምርኮኞቹ ንግግር በተለያዩ አሁን ድረስ የተሳሳተው ትርክት ሰለባና ተጠቃሚ በሆኑት ዘንድ ከፍተኛ ብስጭትን የፈጠረበት ዋነኛ ምክንያት በድርጅቱ ደጋፊዎች ዘንድ የክህደት ስሜትን በመፍጠሩና ለዓመታት የተገነባውን የወታደራዊ ልዕልና ትርክት ባዶነት በማስቀረቱ ነው። ለአስርት ዓመታት “የማይበገሩ፣ ተራሮችን አንቀጥቃጭ” ተብለው ሲወደሱ የነበሩ አዛዦች፣ በተቃራኒው ኃይል ሚዲያ ቀርበው ሲመሩት የነበረውን ትግል “ትርጉም የለሽና የሞኝነት” ብለው መፈረጃቸው፤ በተለይም በጦርነቱ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ላጡ ወገኖች የከፈሉት መስዋዕትነት ከንቱ እንደነበር ስለሚነግራቸው ከፍተኛ ሐዘንና ቁጭት ስለሚፈጥር፣ የተጠቀሱት የትርክቱ ተጠቃሚዎች በንዴት ቢጦፉ አያስገርምም።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሁኔታ በፖለቲካ ተንታኞችና በሌሎች ወገኖች ዘንድ ብስጭትን የሚፈጥረው በአመራሮቹ የኃላፊነት መሸሽ ምክንያት ነው። ጦርነቱን በዋናነት ሲመሩና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ወደ እሳት ሲማግዱ የነበሩት እነዚሁ ከፍተኛ አዛዦች ሆነው ሳለ፣ እጃቸውን ከሰጡ በኋላ የራሳቸውን የአመራር ድርሻና ጥፋት ወደ ጎን ትተው ትግሉን ብቻ መውቀሳቸው “ከተጠያቂነት ለማምለጥ ወይም ምህረትን ፍለጋ የሚደረግ ሙከራ ነው” የሚል ትችት ያስነሳል። በአጠቃላይ፣ የምርኮኞቹ ቃል በአንድ በኩል የዓመታት የፕሮፓጋንዳ ግንብን በማፍረሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጦርነቱን አስከፊነትና የአመራሮቹን ሚና በአደባባይ በማጋለጡ በሁሉም አቅጣጫ ከፍተኛ ስሜታዊ ምላሽና ብስጭትን አስከትሏል።
ሰሞኑን እንደታየው በመጨረሻ እውነታው ሲገለጥና የውሸት ግንቡ ሲናድ፣ የሚፈጠረው የሥነ-ልቦና ስብራት፣ የእርስ በርስ መጠላላትና የሞራል ውድቀት ካለፈው ኪሳራ በላይ አደገኛ ይሆናል። ለዓመታት በውሸት ትርክት የተገነባ ማንነት፣ እውነት ፊት ሲቆም እንደ አሸዋ ላይ የተሰራ ቤት መፈራረሱ አይቀሬ ነው። ይህ የሃሰት ትርክት ሲናድ ወደ እርስ በርስ መጠፋፋት ይሚያመራ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከወዲሁ ጥንቃቄ መወሰድ አለበት።
ለአስርት ዓመታት በህወሓት ፕሮፓጋንዳ መዋቅር ሲገነባ የቆየው የወታደራዊ አመራሮች የጀግንነትና የልዕልና ትርክት፣ ዛሬ በራሳቸው በአዛዦቹ መማረክና በተከታዮቻቸው የእርስ በርስ መወነጃጀል ሲፈራርስ መታየቱ በደጋፊዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንና ድንጋጤን ቀስቅሷል። ቀደም ሲል የድርጅቱ ሚዲያዎችና አቀንቃኞች እነዚህን ጄኔራሎች የሌላቸውን ጀግንነትና የስትራቴጂ እውቀት በመስጠት፣ አልፎ ተርፎም የሰው ልጅን ሕይወት እንደ ቁስ በመቁጠር “ማገዶ ቆጣቢ ጄኔራሎች” እያሉ ሲያቆላምጧቸው ቆይተዋል።
ይህ በሰው ልጆች ደምና ሕይወት ላይ የተመሰረተ የፕሮፓጋንዳ ቁማር ምን ያህል አስከፊ እንደነበር፣ ራሳቸው የድርጅቱ አመራሮች በጦርነቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተዋጊዎቻቸው መሞታቸውን በይፋ ማመናቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይባስ ብሎም፣ ትናንት “የማይበገሩ” ተብለው ሲወደሱ የነበሩት አዛዦች እጅ ከሰጡ በኋላ፣ የራሳቸው ወገኖች የቀድሞ ጓዶቻቸውን “አንድ ገጽ መጻፍ የማይችሉ ደንቆሮዎች” በማለት ማጣጣላቸው፤ ለዓመታት የተነገረው ገድል ባዶ ፕሮፓጋንዳ እንደነበር በማጋለጡ ደጋፊዎቻቸውን ክፉኛ አናዷል።
የኢትዮ ሚዲያ ፎረሙ (EMF) ምስክርነት
በቅርቡ እጃቸውን የሰጡ የቀድሞ የትህነግ ጀነራሎችና ኮሎኔሎች፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛ ማዕረግ የነበራቸው ሰዎች፤ ያደረጉት የትጥቅ ትግል ትርጉም የለሽና የሞኝነት እንደነበር “ከሃዲዎቹ ምርኮኞች” በሚል ርዕስ በመከላከያ ሠራዊት በተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም ላይ መናገራቸው በዲያስፖራው የሚገኙ የትህነግ ደጋፊዎችን ክፉኛ አስቆጥቷል። ለሃምሳ ዓመታት ያህል ትህነግ ታጋዮቹ ሞትን የማይፈሩ፣ “ኮሎኔል ማራኪ”፣ የማይበገሩና “ተራሮችን ያንቀጠቀጡ” እንደሆኑ አድርጎ የገነባው ትርክት በራሱ የቀድሞ አዛዦች አንደበት መፈራረሱ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል። ይህንን የፈራረሰ ትርክት ለመጠገንና የደረሰውን ጉዳት ለመቆጣጠር የኢትዮ ሚዲያ ፎረሙ (EMF) ያየሰው ሽመልስ ባቀረበው ዘገባ፣ እጃቸውን የሰጡትን ጀነራሎች ከመለስ ዜናዊ ለመነጠልና የመለስን ስም ለማዳን ሞክሯል። ይሁን እንጂ ያየሰው መለስ ዜናዊን “ድንቅ አሳቢ” አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር፣ ሳያውቀው የመለስ ዜናዊን ባዶነት፣ የአመራር ድክመትና በጥላቻ የታወረ ማንነት በአደባባይ ራቁቱን አስቀርቶታል።
ራሱን ያጠፋው የማስተባበያ ሙከራ
ያየሰው እነዚህ ከፍተኛ አዛዦች ለምን እጃቸውን እንደሰጡና ትግላቸውን እንደካዱ ለማስረዳት ሲሞክር፣ ሰዎቹ ከመጀመሪያውም እውነተኛ ታጋዮችም ሆኑ አሳቢዎች እንዳልነበሩ ገልጿል። በያየሰው ባቀረበው ጥንቅር ላይ እነዚህ “ጀነራሎች” “በመለስ ዜናዊ አእምሮ እና ትከሻ ላይ ተንጠላጥለው አዲስ አበባ የገቡ”፣ “ትንሽ ፊደል ቆጥረው” በመለስ ዙሪያ የተሸሸጉና “የገበሬ ልጆች እየሞቱላቸው” ከጦር ግንባር ርቀው የኖሩ በማለት ገልጾዋቸዋል።
ያየሰው በዚህም አላበቃም፤ “መለስ ዜናዊ የሚባል ሰው ባይኖር ኖሮ ወላጆቻቸው ብቻ የሚያውቋቸው ሰዎች ይሆኑ ነበር” ሲል ተናግሯል። አክሎም መለስ እያሰበ፣ መለስ እየሰራና “መለስ ጽፎ የሰጣቸውን እያነበቡ” አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ጀነራል አድርጎ እንደመደባቸው፣ እነዚህ ሰዎች ግን “አንድ ገጽ ጽፈው ፖለቲካ እና ውትድርና መስራት የማይችሉ” እና “የሚቆሙለት መርህና አቋም የሌላቸው” መሆናቸውን በአደባባይ መስክሯል። መለስ ዜናዊ: ባዶና በጥላቻ የታወረ፣ ከተከታዮቹ የባሰ አላዋቂና የወረደ “መሪ”
ያየሰው ይህንን የተናገረው እጃቸውን የሰጡትን ጀነራሎች ለማዋረድና መለስ ዜናዊን ብቸኛ ሊቅ አድርጎ ለማጉላት ቢሆንም፣ ንግግሩ በቀላል አመክንዮ ሲመዘን መለስ ዜናዊን ራሱን እጅግ ከንቱና አላዋቂ መሪ መሆኑን አረጋግጧል። የያየሰውን ንግግር እውነት ነው ብለን ከተቀበልን፤ ማለትም እነዚህ ጀነራሎች መርህ የሌላቸው፣ አንድ ገጽ መጻፍ የማይችሉና የማይረቡ ስብስቦች ከነበሩ፤ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ይነሳል፤ እነዚህን ሁሉ ከንቱ፣ ደካማና የማይረቡ ሰዎች በዙሪያው ሰብስቦ የሀገርን መከላከያ ሰራዊት እንዲመሩ ጀነራል አድርጎ የሾመው መለስ ዜናዊ ምን ያህል የወረደ፣ ፈሪ፣ ከጥላቻ በስተቀር ማሰብ የማይችልና ደካማ መሪ ነበር ማለት ነው?
በያየሰው የራሱ ምስክርነት መሰረት፣ መለስ ዜናዊ ነገሮችን አርቆ መተንተን የማይችል፣ ራዕይ የሌለውና በጥላቻና በበቀል ስሜት ብቻ የሚነዳ ግለሰብ ነበር። አንድን ሀገር በብቃት ከመምራት ይልቅ፣ በዙሪያው የሰበሰበው የራሳቸው ሀሳብ የሌላቸውን፣ አንድ ገጽ እንኳን መጻፍ የማይችሉ ደካሞችን ነበር፤ ምክንያቱም ብቁና አዋቂ ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ የእሱን ባዶነትና አምባገነንነት ስለሚገዳደሩት ነበር። የማይረቡ ሰዎችን በዙሪያው መሰብሰቡ የመለስን ሊቅነት ሳይሆን፣ የራሱን አቅመ ቢስነት፣ የስልጣን ጥማትና ለሀገር የነበረውን ጥላቻ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
የሃምሳ ዓመት ተረት ፍጻሜ
ለአስርት ዓመታት ሕዝቡ ሲነገረው የኖረው የትህነግ ወታደራዊ አመራሮች ድንቅ ስትራቴጂስቶችና የማይበገሩ ጀግኖች እንደሆኑ ነበር። ለዚህም ትልቁ ማሳያ የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ ከተማራኪዎቹ አንዱ የሆነውን ዮሐንስ መዲድን “ማገዶ ቆጣቢ” ብሎ ሲያደንቀው የነበረበት የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው፤ እዚህ ላይ “ማገዶ” የተባለው ምስኪኑን ተዋጊ ወጣት መሆኑን ልብ ይሏል። ይሁን እንጂ ራሱ ዮሐንስ መዲድ በዶክመንተሪው ላይ ቀርቦ ሲናገር “አይተነው የማናውቀው መከላከያ ነው የገጠመን፤ ያላሰብነው ጦርነት ነበር” ብሎ መማረኩንና ሽንፈቱን በአደባባይ አምኗል።
ዛሬ ላይ ግን የእነዚህን አዛዦች እጅ መስጠት ለማስተባበል ትህነግ ባደረገው የድንጋጤ ሩጫ፣ በትግርኛ የተጻፈለትን ባማርኛ ተርጉሞ በሚያነበው ያየሰውና በራሱ የትህነግ ሚዲያ እነዚያ ጀነራሎች ከመጀመሪያውም ከንቱ እንደነበሩና መለስ ዜናዊ ጽፎ እየሰጣቸው ኮከብ የደረደረላቸው መሆኑን በአደባባይ አረጋግጧል።
ያየሰው ሽመልስ የመለስ ዜናዊን ስም ለማዳን ሲል የመላውን የትህነግ አመራርና የመለስን ጭንብል ገፍፎታል። መለስ ዜናዊ ሀገርን ሲያምስና ሕዝብን ሲከፋፍል ኖሮ፣ ትቶት ያለፈው ውርስ (ሌጋሲ) የማይረቡ ሰዎችን ስብስብ ብቻ መሆኑን የራሱ ሚዲያ በአደባባይ መስክሯል። ይህም መለስ ሲሞት በስድስት ዓመት ውስጥ እንደ እንቧይ ካብ የተናደ የውሸትና የጥላቻ ግንብ መሆኑን በራሳቸው አንደበት አሳይተዋል






