አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | “ማንኛውም አዲስ ነገር ዕዳም ምንዳም አለው፤ ለሀገር የሚበጀውን መምረጥ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው” ሲሉ ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ። ኢትዮጲያ አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ህዝብ እንደሌላት ሁሉም እንዲያውቀው በኩራት ተናግረዋል።
“ቀይ ባህር ላይ ድርሽ አትልም። አያገባትም። አባይ ላይ ግን እኛ ያገባናል” በሚል ግብጽ የመከሩትን ጨምሮ “ባንዳ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለጠሯቸው እንዲሆን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ በሁሉም አግባብ ዝግጁ እንደምትሆን አመልክተዋ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው የመንግሥት ምስረታ ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አዲስ ነገር ዕዳም ምንዳም ስላለው ለኢትዮጵያ የሚበጀውን መርጦ መከተል የዚህ ትውልድ ኃላፊነት እንደሆነ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ተሸናፊ ዜጋ የማይኖራት፣ አሸናፊ ሕዝብ የሚኖራት ሀገር መሆኗን አረጋግጠዋል። 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝብ የተመረጠበት ሂደት ቀላል እንዳልነበር ጠቁመው፣ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ የሕዝቡ ውሳኔ መገለጹን ተናግረዋል።
ዓለም በፍጥነት እየተለወጠችና አለመገመት በሰፈነበት ወቅት ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ ማቆም ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ዐቢይ አሕመድ፣ ከዓለም የተለያዩ የለውጥና የኢንዱስትሪ ዘመናት ትርፍ ብቻ እንዳይደርሳት ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት ማለትም መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም. በተካሄደው የ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይፋ ሲሆን፣ ፍጹም ብሄራዊ ስሜትን በሚቀሰቅስ እና ዜጎች በያሉበት እንዲወያዩ የሚያስችላቸው ወቅታዊ ጉዳዮችን አንስተዋል። የህገመንግስት ማሻሻያ፣ የቀይ ባህር ጉዞና ሌብነት ላይ መራር እርምጃ እንደሚወሰድ መናገራቸው ተጠቅሷል።
በሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ብልጽግና 438 መቀመጫ በማሸነፉ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች 40፣ ውጭ በግል ያሸነፉ አስራ ሰባት አሸናፊዎች በታደሙበት የመንግስት ምስረታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ በቀጣይ ጊዜያት የሀገራዊ ምክክሩ ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች መሠረት በማድረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደሚደረግ ይፋ ማድረጋቸው የህዝብ ቀልብ ከሳቡ ጉዳዮች ቀዳሚ ሆኗል።
የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ከሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የሚመነጩ ምክረ ሐሳቦችን በመመርመርና በማጤን የሚከናወን መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። በዚህም ሀገራዊ ምክክሩ ያነሳቸው የሀገር ግንባታና የፖለቲካ ሥርዓት ጉዳዮች በቀጣይ በሕግና በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሂደት ውስጥ ሊካተቱ እንደሚችሉ አመላክተዋል።
“በሌብነት ላይ መንግሥት መረር ያሉ እርምጃዎችን ይወስዳል” ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ሌብነት የስርዓቱ አሳሳቢ ችግር መሆኑ በስፋት እና በገሃድ እየተገለጸ ከመሆኑ አንጻር ሌላው ከንግግራቸው የሚጠቀስ ጉዳይ ሆኗል። በአገሪቱ በሚዲያና በመሸፋፈን የሚከናወነውን የቡድን ዘረፋ፣ የዘመቻ እና የጥድፊያ ፕሮጀክቶች አስመልክቶ ከየአቅጣጫው ወቀስ የሚሰነዘርበት የብልጽግና መንግስት ሌብነትን ደረጃ ሳይለይ ሊዋጋ እንደሚገባ ዜጎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚያሳስቡት ጉዳይ ነው።
በዛሬው የመንግሥት ምስረታ ጉባኤ ላይ ቃለ መሐላ የፈጸሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ሙስናን፣ ሌብነትን፣ የዘመኑን የማይመጥን አሠራርና ወገንተኝነትን ለማስወገድ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ መግለጻቸው በመደጋገሙ “መንግስት ሌብነት ላይ እንዴት እንደሚያመር ለማየት ቸኩለናል፤ ሌብነት ላይ አምርሮ ያሳየን” ያሉ በዝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደራቸው የተቀላጠፈና ዘመናዊ የአገልግሎት አሠራር ለመገንባት በትጋት እንደሚሠራ ጠቁመዋል። በተለይም ሙስናና ወገንተኝነትን የሚያበረታቱ አሠራሮችን ለመቅረፍ አስፈላጊው ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጽናት በማንሳት፣ “ውድቀቷን ሲያስቡ ትነሣለች፤ ድክመቷን ሲናፍቁ ጠንክራ ትወጣለች፤ ተበተነች፣ አለቀላት ብለው ሳይጨርሱ ተሰብስባ ትገኛለች” በማለት፣ “የኢትዮጵያ ነገር ትንግርት ነው” በማለት ከነማስረጃውና ማብራሪያ መናገራቸው የዛሬ ንግግራቸው ቁንጮ አሳብ ሆኗል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አቅራቢነት በድጋሚ ኢትዮጵያን እንዲመሩ የተመረጡት አብይ አሕመድ፣ ባደረጉት ንግግር በአገራዊ፣ ቀጠናዊ እና የውጭ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ በርካታ ቁምነገሮችን አንስተዋል። በተለይም ኢትዮጵያን ለማሽመድመድ የተደከመውን ድካም ዘርዝረው “ትፈርሳለች ያሏት አገር ዛሬ የቀጠናው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆናለች” በማለት ሲናገሩ ፓርላማው አጨብጭቦላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባሕር፣ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን “የለውጥ ማዕበል” ያነሱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ወሳኝ (አንከር) ሚና እንዳላት ያመለከቱት በኩራት ነበር። ኢትዮጲያ ላይ ለማበር የተሰባሰቡ ግንባር ፈጥረው ኢትዮጵያን ለማወክ በሚሯሯጡበት ወቅት “ኢትዮጵያ የሚያውኳትን ሁሉ ታሸንፋለች” በማለት የቀደሙ አባቶችን ጀግንነት በማውሳት ሙሉ እመነታቸውን አሳይተዋል። ኢትዮጵያ የዘመነ፣ ዘመኑን የሚዋጅ፣ ሃይል እንደሚኖራትም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን ውድቀት የሚመኙ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ጥረት አለመሳካቱን ሲያስረዱ፣ “ውድቀቷን ሲመኙ ትነሳለች፤ ተበተነች አለቀላት ብለው ሳይጨርሱ ተሰብስባ ትገኛለች፤ የኢትዮጵያ ነገር ትንግርት ነው” ብለዋል። ኢትዮጵያ በቀጠናው ወሳኝ አገር መሆኗን ሲያስታውቁ ይህ በሰዎች ችሮታ ሳይሆን በራሷ ጉልበትና ፍላጎት የምታረጋግጠው ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህንን ሲሉ ፓርላማው በኩራት አጨብጭቦላቸዋል።
“የጠላቶቻችን ትኩረት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እንዳትነግሥ መገደብ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ዘላቂ ችግር የሚፈታው ሥልጣኔ ስትገነባ መሆኑን እና ይህ ሥልጣኔ ደግሞ “ያለ ባሕር በር እውን ሊሆን እንደማይችል” አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር እና ወጥቶ መግቢያ የማግኘት ጥያቄዋ በ”ሰጥቶ መቀበል” መርሕ መልስ እንዲያገኝ መንግሥታቸው ተግቶ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የመንግሥታቸውን ቀጣይ አቅጣጫዎች ሲገልጹ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን፣ የውይይት እና የይቅርታ መንገድ እንደሚከተሉ፣ የመገናኛ ብዙኃን ምኅዳሩ ሕግን፣ አገራዊ እሴትን እና ፍላጎትን ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀስ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በጫካ የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አገሪቱ ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር እንደምትሠራና የውጭ ግንኙነቱም የኢትዮጵያን ተጽዕኖ በሚያሳይ መልኩ እንደሚቃኝ ገልጸዋል። ወቅታዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩም የአየር ኃይልን ጨምሮ ዘመናዊ የመከላከያ ኃይል የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
አብይ አሕመድ ከለውጡ በኋላ በኢኮኖሚ፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰሩ ስራዎችን፣ በከተማ ልማት፣ በታላላቅ ግድቦች፣ በተጀመሩ ወሳኝ የልማት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ወዴት እንደምትሮጥ የገባቸው ለማሰናከል የሚያደርጉት ሩጫ እንደማይሳካ ደጋግመው አመልክተዋል። አክለውም እንደማይሆንላቸውና እንደሚሸነፉም አስታውቀዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






