ታዬ አጽቀ ሥላሴ”በታማኝንት፣ በጨዋነት፣ በታታሪነት አገልግሉ” የሚል ጥሪ አሰሙ፤ የባህር በር ጉዳይ የኢትዮጵያ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን አስታወቁ

Date:

አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የህዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ስፋት የሚመጥን አስተማማኝ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አረጋግጠዋል። በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም በተመሳሳይ ይህንኑ ማለታቸው አይዘነጋም፤ ፕሬዚዳንቱ ይህ የባህር በር ፍላጎት በማናቸውም መልኩ በኃይል ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ፣ በዲፕሎማሲያዊ ድርድር እና በዓለም አቀፍ ህግጋት መሠረት የጋራ ተጠቃሚነትን (Win-Win) ባረጋገጠ መልኩ እንደሚከናወን አፅንዖት ሰጥተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የታላቁ ህዝብ ምክር ቤት የመንግስት ስልጣን መሰረቱ እና ምንጩ የሰፊው ህዝብ የይሁንታ ድምጽ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሕያው ምስክር እንደሆነ አመልክተው ለመንግስት እቅድ ተፈጻሚነትና ለህዝብ ጥቅም ሲባል በቁርጠኛነት፣ በጨዋነት፣ በጽናት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የህዝብ ምክር ቤት አባላት የሚያከናውኗቸው ተግባራት እና የሚደነግጓቸው ህጎች በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የስልጣን ፍኖት በህዝብ የይሁንታ ድምጽ እና ተቀባይነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አመልክተው፤ ሕዝብ የጣለባችሁ ሀገራዊና ህዝባዊ ሀላፊነት በእጅጉ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ስለዚህ የህዝቡ ይሁንታ ከአመኔታ ጋር ታላቅ አደራን መስጠቱን እንደሚያረጋግጥ አመልክተው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ሀላፊነት በታላቅ አስተዋይነት፣ ጥበብ፣ ብልሃትና ታታሪነት እንደምትወጡት ያምናል ብለዋል። ሁለንተናዊ ዝግጅታችሁ ይህንን አደራ የሚመጥን ብቻ ሳይሆን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ጭምር ሊሆን ይገባል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው።

የምክር ቤት አባላቱ ቀዳሚ ትኩረት መልካም አስተዳደርን የሚያዘምን፣ የሀገራችንን ኢኮኖሚ በይበልጥ ከፍ የሚያደርግ፣ ምርት እና ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ የኑሮ ውድነትን የሚገራ፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ይበልጥ የሚያስፋፋ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በስፋት የሚዘረጋ፣ የህዝብን ሰላም እና ደህንነት የሚያጸና መሆን እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

“ብሔራዊ አንድነትን እና ሰላምን የማፅናት ጉዞ” አስመልክቶ በሀገሪቱ ውስጥ ሕጋዊ የኃይል አጠቃቀም ሥልጣን የመንግሥትና የመከላከያ ኃይሉ ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል። በትጥቅና በኃይል የፖለቲካ ፍላጎትን ለማስፈጸም የሚደረጉ ጥረቶች ከእንግዲህ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌላቸውና መንግሥት ለዚህ ጉዳይ በቂ ጊዜ ሰጥቶ ማለፉን በግልጽ ተናግረዋል።

መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጠኛ ቢሆንም፣ ለማንኛውም ሰላማዊ አማራጭ የሰላም በሮች ሁልጊዜም ክፍት መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ከማንኛውም የታጠቀ ቡድን ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገርና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅና ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዜጎች መካከል ዘላቂ ብሔራዊ መግባባትን፣ አንድነትንና የጋራ ራዕይን ለመገንባት መሠረት እየጣለ እንደሚገኝ አፅንዖት ሰጥተዋል።

የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ለማስከበር፣ የዜጎችን የደህንነትና የሰላም መብት ለማረጋገጥ የጸጥታ ኃይሎች እያበረከቱት ላለው ታላቅ አስተዋጽኦ እና መስዋዕትነት እውቅናና ምስጋና ሰጥተዋል። ለአገር መከላከያ አባላት ምክር ቤቱ በጭብጨባ ክብር ሲሰጥ ታይቷል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ በሀገሪቱ የተመዘገቡ ዋና ዋና የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ አፈጻጸሞች እንዲሁም ለቀጣይ የሥራ ዘመን የተያዙ ቁልፍ አቅጣጫዎችን ይፋ አደርገዋል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው መጀመሪያ ላይ የምክር ቤት አባላት የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ የሆነውን የሕዝብ ውክልና በመያዝ መልካም አስተዳደርን የማስፈን፣ የኑሮ ውድነትን የመግራት፣ የምርት ዕድገትን የማረጋገጥ፣ እንዲሁም ሰላም እና ደኅንነትን የማጽናት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በክፍለ ጊዜው የቀረቡትን የተመዘገቡ የኢኮኖሚና የልማት አፈጻጸሞች ስንመለከት፣ ሀገራዊ የሰብል ምርት ወደ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ማደጉ ተገልጿል።

የወጪ ንግድ ገቢ 11.2 ቢሊዮን ዶላር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም አጠቃላይ የታክስ ገቢ 1.18 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። በተጨማሪም የዋጋ ግሽበት ወደ 13.4 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተመላክቷል።

ጊዜ እና ሀብት ያባክኑ የነበሩ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ ማጠናቀቅ መቻሉ፤ እንዲሁም የከተማ ኮሪደር ልማትና የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮጀክቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ አብነት የሚሆኑ ስኬቶች ሆነው መመዝገባቸው ተጠቅሷል።

በሰላም፣ ፖለቲካ እና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ፣ የጠመንጃ ባህል እና የነፍጥ አዙሪትን በዘላቂነት በማስቀረት የፖለቲካ ልምምዱን በሰላም፣ በንግግር እና በመደማመጥ ላይ መመሥረት፤ እንዲሁም በሀገራዊ ምክክር ሂደት የተገኙ የውይይት ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር ቅድሚያ ተሰጥቷል።

የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ሀገራችንን ከተቀባይነት ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እያሸጋገራት መሆኑ፣ እንዲሁም አስተማማኝ የባሕር በር ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በሰላማዊ መንገድና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ተብራርቷል።

ለቀጣይ የሥራ ዘመን የተያዙ ዋና ዋና ግቦችን በተመለከተ፣ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱን 10.1 በመቶ ማድረስ እና የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ማድረግ ታቅዷል። ከዚህ ባለፈ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን 65 በመቶ፣ የጤና መድኅን ሽፋንን 85 በመቶ፣ የተማሪዎች ምገባ ሽፋንን 70 በመቶ ማድረስ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ኃላፊነት የወሰደችበትን 32ኛውን የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32) በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት፣ እንዲሁም በበጀት ዓመቱ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ የውጭ ቱሪስቶችን ለመሳብ ግብ ተቀምጧል።

በመጨረሻም የተጀመረውን የፀረ-ሙስና እና ሌብነት ትግል አጠናክሮ መቀጠል፣ የመከላከያ እና የጸጥታ ተቋማትን አቅም መገንባት፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ቅንጅትን ማሳለጥ፣ እንዲሁም የታክስ አስተዳደርን በማዘመን የመንግሥትን ወጪ እና ገቢ በአግባቡ መቆጣጠር የመንግሥት ቁልፍ አቅጣጫዎች መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።

ሰላም ለኢትዮጵያ እድገት እና ብልጽግና ያለው ዋጋ ያጤነና እና ከማንኛውም ጊዜ የበለጠ ህብረትን፣ ትብብርን እና ኢትዮጵያን የሚያስቀድም ተግባር የሚከናወን ይሆናል። ጥራትን መሰረት ያደረገ ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲኖር ይደረጋል። ትምህርት፣ ጤና እና ማህበራዊ ጥበቃን ከስፋት ወደ ጥራት በማሸጋገር ዜጋን ማዕከሉ ያደረገ ልማት ይፋጠናል።

ለእድገታችን ቁልፍ ፋይዳ ባላቸው የኢንዱስትሪ እና የግብርና ግብአቶች እንዲሁም ዘመናዊ የመሰረተ ልማት ግንባታ አቅማችን ራሱን እንዲችል ይደረጋል። የፕሮጀክት እና የፕሮጀክት ፋይናንስ አፈጻጸም ዘመናዊ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ይሰራል።

የታክስ መሰረትንም በማዘመን፣ ዕዳን ወግ ባለው መልኩ ማስተዳደር እንዲሁም የመንግስት ገቢ እና ወጪን በአግባቡ የመቆጣጠር አቅም ያድጋል። በፌደራል መንግስት እና በክልሎች መካከል ያለው የሰራ ቅንጅት እና የአፈጻጸም ኩነት የተባበረ፣ የተደጋገፈ፣ ቀልጣፋ እና እንከን አልባ እንዲሆን ይደረጋል።

የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ከተቀባይነት ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያሻግር፣ በተለይም ወዳጆችን በማበራከት የሚተጋ፣ የደመኝነት እይታ ያላቸውን ደግሞ የሚመክር፣ ለቀጣናዊ ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ምንጊዜም ቅድሚያ የሚሰጥ ተነሳሽነቶች ያሉት እና አለም አቀፍ ተቀባይነታችንን የሚያሳድግ ይሆናል። #የመደመር_መንግሥት

ምክር ቤት አባላት የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ የሆነውን የሕዝብ ውክልና በመያዝ መልካም አስተዳደርን የማስፈን፣ የኑሮ ውድነትን የመግራት፣ የምርት ዕድገትን የማረጋገጥ፣ እንዲሁም ሰላም እና ደኅንነትን የማጽናት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል::

ሀገራዊ የሰብል ምርት ወደ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ማደጉ፣ የወጪ ንግድ ገቢ 11.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4.5 ቢሊዮን ዶላር መመዝገቡ፣ አጠቃላይ የታክስ ገቢ 1.18 ትሪሊዮን ብር መድረሱ እና የዋጋ ግሽበት ወደ 13.4 በመቶ ዝቅ ማለቱን አንስተዋል

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related