አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ |ሻዕቢያ ያደራጀው የዋሽንግተኑ ሰልፍ የፅምዶን ባለቤት ማን መሆኑን በይፋ አረጋግጠ፤ ኢትዮጵያዊያን “አገራቸውን ለሽያጭ አያቀርቡም” ተባለ፤ የትግራይ ወጣቶች እንዳደረጉት ሻዕቢያ ወጣቶች ተለዩት። ሻዕቢያ ባዘጋጀው በዋሽንግተኑ ሰልፍ የጽምዶ ባለቤት እና አጃቢዎች በይፋ ታሪክ ፊት መቆማቸውን ታዛቢዎች አስታወቁ። “ክህደትን ክራባት ለብሶ አየነው” በማለት የተገረሙ ተናገሩ።
በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በትናንትናው ዕለት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አካባቢ የተካሄደው ሰልፍ፣ የታሰበው ኢትዮጵያዊያን በብሄር ብሄረሰብ ተከፋፍለው የሻዕቢያ ደጋፊ በመሆን አገራቸውን እንዲያወግዙ ነበር።
ከሰልፉ በፊት የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ ካነጋገራቸው መካከል “ከጥቂት እንክርዳዶች በስተቀር ኢትዮጲያዊያን አገራቸውን ለሽያጭ አያቀርቡም” ብለዋል። “አንዳንድ ፍርፋሪ ለቃቃሚዎች ጊዜያዊ የፖለቲካ ልዩነትን አገራቸውን ለሚያፈርስ ቡድን በመገረድ መጠቀሚያ ያደርጋሉ” በማለት ከሻዕቢያ ስር ስር የሚሉትን በስም ጠርተው ኮንነዋል።
“ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በመሰረተው ጽምዶ ውስጥ የተሰባሰቡና እና አጃቢዎች በይፋ ታሪክ ፊት ቆሙ” ያሉት አስተያየት ሰጪዎች “ግርድና ቢያምራቸው እንኳን እንዴት ከሻዕቢያ ደጅ ያደርጉታል” በማለት መገረማቸውን ገልጸዋል። አቶ ይገረም የተባሉ “ሻዕቢያን በየትኛውም ሂሳብ አምኖ የሚንበርከክ ኢትዮጵያዊ ማሰብ ስለመቻሉ እጠራጠራለሁ” ብለዋል። አክለውም “ክህደት ክራባት ለብሶ አየሁት። አይ ዘመን” ሲሉ ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
ሰልፍ እንዲወጡ ተጋብዘው እንደነበር አመልክተው “እኔ ፖለቲካና አገርን ለይቼ የማይ፣ ብሄራዊ ጥቅም ላይ የጸና አቋም እንዳለኝ፣ ከምንም በላይ ሻዕቢያን ጠንቅቄ ስለማውቅ እሱ አለበት ስፍራ ድርሽ የማልል ኩሩ ኢትዮጵያዊ እንጂ ለራሱም ከሌለው ጠኔያም ድርጅት ደጅ የምለቃቅም ሰው አይደለሁም” በማለት ክፉኛ ተቆጥተው ምላሽ እንደሰጡ አምልክተዋል።
እኚሁ አስተያየት ሰጪ “እድሜውን ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ተቃዋሚ ሲያደራጁ የኖሩት የባንዳዎችና የተላላኪዎች አለቃ የሆኑት ኢሳያስ ጸሎታቸው ሁሉ ‘ኢትዮጵያን ስላፈራርስ አትውሰደኝ’ ነውና ኢትዮጵያዊያን በርጋት ነገሮችን እንመርመር” በማለት ትራፊ ለቃቃሚዎች ያሏቸውን እንዳይሰሙ አሳስበዋል።
በሰልፉ ላይ ከተገኙት ጥቂት ሰልፈኞች በስፋት የታየው የኤርትራ ባንዲራ ሲሆን አልፎ አልፎ የህወሓት እንዲሁም የህወሃት ደጋፊዎች ከሆኑ መካከል የኮከብ ምልክት የሌለውን የኢትዮጵያን ባንዲራ በቁጥር ከሁለት የማይበልጥ ይዘው ታይተዋል። ከሰልፉ በላይ መነጋገሪያ የሆነው “ህወሃት እና ሻዕቢያ የጨው መቋጠሪያ” ያሉትን የኢትዮጵያ ባንዲራ መሸከማቸው ነው።
በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደው ሰልፍ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶችን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና በቀጣናው የሚታዩ የደኅንነት ስጋቶችን በማንሳት የአሜሪካንና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ትኩረት ለመሳብ የተዘጋጀ እንደሆነ ሰልፉን ያዘጋጀው ሻዕቢያ ንግግር እንዲያደርጉ የመደባቸው አመልክተዋል።
ሰልፉ ሳይጀመር የከሸፈ እንደነበር፣ ኢትዮጵያዊያን በሰልፉ እንዲገኙ በአውደ ምህረትና በቤት ለቤት ሳይቀር ሲቀሰቀሱ “ዘወር በሉ” ማለታቸውን እና “ሻዕቢያን ደግፋችሁ ኢትዮጵያን ወራሪ በሉ” በማለት የቀረበላቸውን ጥሪ “ጸያፍ እና ሊረሳ የማይችል ጥቁር ታሪክ” ያሉንን ጠቅሰን አስቀድመን መዘገባችን አይዘነጋም።
ሰልፉ ከመካሄዱ በፊት ባለፈው ረቡዕ የጋራ መድረክ በሚባለው የአቶ ነዓምን እና የአቶ ልደቱ ጥምረት ስብሰባ ላይ አምስት ሰዎች ብቻ ተገኝተው ስለ ስልፉ ሲወያዩ የተነጋገሩትን በማንሳት እንዳመለከትነው ሻዕቢያ ሰፊ ሃብት መድቦ ነበር። ይህንኑ አስመልክቶ የብርጌድ ንሓምዱ አመራርም ገንዘብ መመደቡን እንደሚያውቁና በሰልፉ እድሜያቸው የገፋ ኤርትራዊያን “ንብረታችን ይነጠቃል” በሚል ስጋት እንደሚሰለፉ መናገራቸውን አትመን ነበር።
የሰልፉ አዘጋጆች በአስቀድሞ ባወጡት የሚዲያ ጥሪ አፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሞ፣ ትግራይና ሶማሌን ጨምሮ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች፣ ከኤርትራ፣ ሱዳንና ሶማሊያ የመጡ የዲያስፖራ አባላት እንደሚሳተፉ አስታውቀው ነበር። ይሁን እንጂ እንደተባለው ሳይሆን በሰልፉ ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የኤርትራ እድሚያቸው የገፋ ሰዎች ሲሳተፉ የተቀሩት ተመሳሳይ እድሜ ያላቸው የህወሃት፣ የሱዳን፣ አልፎ አልፎ ራሳቸውን “ኢትዮጵያዊ” የሚሉ እና አማራውን እንደሚወክሉ የሚናገሩ እጅግ ጥቂት ሰዎች ለሻዕቢያ ሲዘመሩ ታይቷል። ጃልመሮ የሚመራው ኦነግ በቁጥር ተነቅሰው የሚጠሩ ሰዎች ታይተዋል።
ባለፈው ሳምንት ሲውዘርላንድ፣ አሁን ደግሞ አሜሪካ በተደረገው ኢትዮጵያ ላይ ተቃውሞ የማሰማት ዘመቻ፣ የኤርትራ ወታቶች አለመገኘታቸው፣ ህወሃት ከገጠመው ሽንፈት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ተደምጧል። አሊቴና ተራራ ላይ የመሸጉት የህወሃት አመራሮች ወጣቱ “አንዋጋም” በማለት ጀርባውን እንደሰጣቸው ዓይነት የኤርትራ ወታቶች በስለማዊ ሰልፎቹ ላይ አለመገኘታቸው በኤርትራ ለውጥ እንደሚፈለግ አመላካች እንደሆነ የብርጊድ ንሓመዱ አመራር አስታውቀዋል። በመሬት ላይ ያለው የኤርትራ ሰራዊትም ሆነ ወጣት መውጪያ ቢያገኝ ሙሉ በሙሉ ሻዕቢያን ጥሎ እንደሚወጣም አመልክተዋል።
የባንዲራዎች ስብጥር ምን ያሳያል?
ሰልፉን አስመልክቶ በተሰራጨው ቪዲዮ መሠረት፣ ከታዩት ባንዲራዎች ሁለት ሦስተኛ ያህሉ የኤርትራ ባንዲራዎች ሲሆኑ፣ 30 በመቶ ገደማ ደግሞ ከህወሓት ጋር የተያያዙ ባንዲራዎች እንደነበሩ ለመረዳት ተችሏል። የሌሎች ቡድኖች ባንዲራዎች ድርሻ አነስተኛ በመሆኑ ለስሌት ወይም በመቶኛ ማስቀመጥ ይከብዳል።
በዚሁ መሰረት ከአማራና ከኦሮሞ ማኅበረሰቦች የተወከሉ ሰዎች ቁጥር ሰልፉ ከመደረጉ በፊት ሰልፉን ያዘጋጀው ሻዕቢያ የሚደጉማቸውና ያደራጃቸው ሚዲያዎች እንዳሉት ሆኖ አልመታየቱ፣ ከአፋር፣ ከሶማሌ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከአማራና ከሌሎች ማኅበረሰቦች ሰፊ ተሳትፎ ለማምጣት የቀረበው ጥሪም የተሳካ አለመሆኑን ቢያንስ የአሜውሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደጅ የወጣው ባንዲራ ያሳብቃል።
የፅምዶ ጥረትና የቀጣናዊ ፖለቲካ ግንኙነት
የዋሽንግተን ሰልፍ ከተራ የዲያስፖራ ስብሰባ በላይ የፖለቲካ ይዘት ያለው ዝግጅት መሆኑን የተለያዩ ምልክቶቹ ያመለክታሉ። በተለይም ከኤርትራና ከህወሓት ጋር የተያያዙ ባንዲራዎች በብዛት መታየታቸው በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን የኃይል አሰላለፍ የሚያሳይ ሆኗል። ይህም ቀደም ሲል ሻዕቢያ የጽምዶ ፈጣሪ እንደሆነና ይህ ጥምረት የተፈጠረው ሻዕቢያን ለማዳን ተብሎ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የነበረውን የሚያረጋግጥ፣ አላምን ላሉ ማስረጃ ሆኖ የቀረበ እንደሆነ ተመልክቷል።
ጽምዶ ሲቋቋም ይፋ የሆነው ድረገጽ ላይ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ፋኖ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ ሶማሌ፣ ወዘተ አባል መሆናቸውን እና ጥምረቱ የተቋቋመው ሱዳን እንደሆነ በይፋ ሲገልጽ፣ የድረ ገጹ አስተዳዳሪ ኤርትራዊ መሆናቸው በይፋ ከምስላቸው ጋር ይፋ መደረጉ አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችን በአንድ የፖለቲካ አጀንዳ ስር ለማሰባሰብ የሚደረግ ጥረት በቀጣናዊ ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር ውስጥ የሚኖረው ትርጉም ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ ሻዕቢያ የፅምዶ ስብስቡን በመፍጠርና በማስተባበር ሚና አለው የሚለው ክስ በዚህ ሰልፍ ይፋ እንደሆነ ተመልክቷል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






