የተከታዮቻቸው ብዛት ከፍ ያለ ከሆነ ደላሎች በጀት ይዘው “የገጽታ ግንባታ” ዜና ይዘው ይሮጣሉ። እነዚህ የዝናና ክብር ጠባቂዎቹ፣ የዝና ግንባታ ዘርፉን የሚሾፍሩት ሲሆኑ፣ በተቃራኒ “እገሌ እንዳይነካ፣ እገሌ ተነካች” በሚል ሰይፍ የሚያስመዝዙ “የባለሃብት፣ የባለስልጣንና … እልፍ አስከልካዮች” አሉ። ሚዲያው ከጥቂት ኢትዮጵያን ከሚወዱ በስተቀር “አገራቸው ላይ ዘመቻ እና ብሄራዊ ውድቀት የሚያውጁ፣ በአበልና በልዩ ክፍያ በአገር ጥቅም ላይ የሚቆምሩ የሚሾፍሩትም ነው። በኢትዮጵያዊነት ስም ተጠቅልለው ለጠላት የሚተውኑና “በኮድ የታሰረ” መርዝ የሚረጩ “እባጭ ሚዲያዎችም” አሉ። ህግ ዝም ያላቸው አዲስ አበባ ተቀምጠው ለጠላቶቿ የሚሰሩም አሉ…. የሚያሸማቅቁና ከፋዮቻቸው ሲነኩ ቤት ድረስ ዘልቀው በመግባት ቤተሰብን ህጻናት ሳይቀሩ የሚወቅጡና የሚያስወቅጡ …. ዘርፉ በመከራ የታጠረ ነው።
መግቢያ
አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | አገራዊ ፈተና የሆነውን ሌብነት ወይም ሙስናን ለመዋጋትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የማይደለል ሚዲያ የማይተካ ሚና አለው። በኢትዮጵያ የሚታየው የሚዲያ ቁመና በአብዛኛው ሕዝብና ብሔራዊ ጥቅምን ከመጠበቅ (Watchdog) ይልቅ በተቃራኒው መድረክ ሲተውን ይታያል። ይህ ሲባል ጥቂት ራሳቸውን ነጻ አድርገው ለመስራት የሚጣጣሩ የሉም ማለት ግን አይደለም። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ለአገር፣ ለሕዝብና ለብሔራዊ ጥቅም መከራ የሆኑት ላይ ማተኮር ይሆናል።
ከመንግሥት በላይ «መንግሥት» ለመሆን መከራቸውን የሚያዩ፣ ጭልጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ወይም የግለሰቦች፣ የአንዳንድ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች የስብዕና ግንባታ (Cult Building) ገንቢ፣ ጥቅም አስጠባቂ፣ ዝናና ክብር ተከላካይ፣ ወዘተ. ሆነው ይታያሉ። ለዚህም ተግባራቸው ክፍያ የሚፈጸምላቸው፣ በጀት የሚመደብላቸው፣ አቀባባይ ደላሎች የሚያሰማሩ ወዘተ. የሚታወቁ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች እንዲሁም «ተቃዋሚ» የሚባል ስም ያላቸው «ኤጀንቶች» እንዳሉ የተደበቀ አይደለም።
በጥቅም በሚጋሯቸው አማካይነት በሚመደብ በጀት በመደበኛ ሚዲያዎችና በማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች የገጽታ ግንባታ ዘመቻዎች የሚካሄዱላቸው፣ እንዳይነኩ አጥር የሚሰራላቸው የሚዲያ ሠራዊት ከገነቡት ጀምሮ በኢቨንት ስም ጋዜጠኞችን «ጭጭ» ወይም «የራሳቸው ሕዝብ ግንኙነት» የሚያደርጉ የመንግሥት ተቋማት ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሆኑ አሳሳቢ መሆኑን አካሄዱ ያላማራቸው የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች «የመንግሥት ያለህ» እያሉ ነው። የዚህ ጽሑፍ መነሻም ይህ ነው።
«ኢቨንት ሲኖር ለሚዲያዎች የግብዣ ደብዳቤ ወይም መልዕክት መላክ የተለመደ ነው» የሚሉ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች፣ ግብዣው የደረሳቸው ሚዲያዎች እገሌ ከእገሌ ሳይባሉ አበል ስንት እንደሆነ፣ የስንት ቀን እንደሚከፈል፣ አዳር መሆኑን፣ ወዘተ. መጠየቅ የሥራቸው መጀመሪያ ነው።
በዚሁ መሠረት መረጃ ከሰበሰቡ በኋላ ራሳቸው አዘጋጆች ወይም ሪፖርተሮች ወደ ኢቨንቱ ይሄዳሉ። የሄዱበት የሚዲያ ተግባር ካለቀ በኋላ «ኢቨንቱን ያዘጋጁት አካላት ክፍያ የሚፈጽሙት፣ ኢቨንቱን አስመልክቶ የተሠራውን ሪፖርት ሊንክ ተቀብለው ካነበቡ በኋላ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ» የሚሉት የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ተቋማት ሚዲያውን በዚህ መልኩ እንደሚደልሉ ይፋ አድርገዋል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የአንድ ታዋቂ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ «ጥቅሙ ከፍ ካለ አላቆይም፣ ግብዣውን ለሌላ አልሰጥም፤ ወይም በመቀራረብ እንጠቀምበታለን» በማለት በሚሠራበት ተቋም ያለውን ችግር ይናገራል። «አበል ካለው የኑሮ ውድነትና የገቢ እጥረት አንጻር የሚወደድ ቢሆንም፣ እየተለመደ ያለው ነገር የሚዲያውን ልሳን የሚዘጋ፣ የጋዜጠኛውን ነጻነት የሚጋፋ፣ ሚዲያዎች የማስታወቂያ ይዘት እንዲኖራቸው የሚያደርግ፣ የመንግሥት ተቋማትን ላልተገባ ወጪ የሚዳርግ ስለሆነ በሁሉም አግባብ ሊመረመር ይገባል። መፍትሔም ያሻዋል» ብሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህንን እውነታ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ስናነጻጽር፣ ነጻ ሚዲያን በማጠናከር የተሳካላቸው እና በጥቅም ላይ ተመሥርተው ሚዲያውን የመቆጣጠር (Media Capture) ተጠልፈው የተዳከሙ አገራት ልምድ ግልጽ ትምህርት ይሰጣል።
በበጎ የሚጠቀሱ አገራት፡ ደቡብ ኮሪያ፣ ኖርዌይ
በእነዚህ አገራት የሚዲያው ዋና ተልዕኮ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ በሥልጣን ተጠቅመው የሚባልጉትንና የሕዝብ ሀብትን በገለልተኝነት መቆጣጠር ነው። የገቢ ምንጫቸው ከአርትዖት ጣልቃ ገብነት በጸዳ ግልጽ የንግድ ማስታወቂያ፣ በአንባቢና በተመልካች ድጋፍ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ከገንዘብ ድለላ ነጻ ነው። ግለሰቦችን ከተጠያቂነት በላይ አድርጎ ከማሞገስ ይልቅ ተቋማዊ አሠራርንና የሕግ የበላይነትን ያስቀድማሉ። በዚህም ከፍተኛ የፖለቲካና የንግድ ሙስና ቅሌቶችን በምርመራ በማጋለጥ ተጠያቂነትን ያሰፍናሉ፤ የሕዝብ አመኔታንም ያጎለብታሉ፣ ብሔራዊ ጥቅምም ይጠበቃል። በጥቅሉ የተቋማት ወይም የባለሥልጣናት አለቅላቂዎች አይደሉም።
በውድቀት የሚጠቀሱ አገራት፡ ቬንዙዌላ፣ ሃንጋሪ፣ ቡልጋሪያ
በእነዚህ አገራት ሚዲያው የሕዝብን ሐቅ የማወቅ መብት ከማስከበር ይልቅ የፖለቲካ ቡድኖችንና ከሥልጣን ጋር የተቆራኙ ባለሀብቶችን ጥቅም ማስጠበቂያ መሣሪያ ሆኗል። የማስታወቂያና የገንዘብ በጀቶች ለታማኝ አውታሮች ማዘንበልና የባለሀብቶች ባለቤትነት መስፋፋት የሙያውን ነጻነት አዳክሞታል። በዚህም ምክንያት መሪዎችንና ባለሀብቶችን የማሞገስ አዝማሚያ ሲያይል፣ ሙስና ይሸፋፈናል ወይም ለፖለቲካ ተቀናቃኞች መጠቃቂያ ብቻ ይሆናል። ውጤቱም የሕዝብ አመኔታ መሸርሸር፣ የመረጃ መዛባትና የተቋማዊ ተጠያቂነት መዳከምን ያስከትላል።
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ
በኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳሩ በመንግሥት፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በባለሥልጣናትና በባለሀብቶች የጥቅም አሰላለፍ በመከፋፈሉ ሙያዊ ገለልተኝነት ተዳክሟል። ለገጽታ ግንባታ በተያዘ በጀት (Paid PR) እና ዜናው ተሠርቶ ሊንኩ ከተላከ በኋላ በሚከፈል አበል መደለል እየተለመደ መጥቷል። በተለይም ለአንዳንድ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ልዩ በጀት ተይዞ የግል ዝናና ከለላ (Cult Building) የመገንባት ሂደት እውነተኛ የሙስና መረጃዎች እንዳይጋለጡ እንቅፋት ሆኗል። በዚህም ብሔራዊ አጀንዳ ከግልና ከቡድን ጥቅም ጋር ተቀላቅሎ አገርን ለአደጋ እያጋለጠ ይገኛል።
ሕዝብ በገሃድ እንደሚያየው ጽንፍ ወጥተው የሕዝብን ሰላም የሚነሡ፣ ለተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች በመወገን የተጠኑ እና በኮድ የሚሰራጩ አጀንዳዎችን ከሚሰፍሩ ጀምሮ፣ ከዚያ ወገን ያልሆኑትን የሚፈርጁ፣ የሚያሸማቅቁ፣ እስከ ትዳርና ተራ የቤት ጉዳይ በመግባት የሚያቆሸሹ ሚዲያዎች፣ «እገሌ ወይም እገሊት ለምን ተነካች» በሚል የስድብና የዘለፋ ውርጅብኝ የሚያወርዱ የማኅበራዊ ሚዲያ ሠራዊት የሚያዘምቱ እጃቸው ረጃጅም «ከፋዮች» በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ማየት እንግዳ አይደለም።
ከንጽጽሩ የሚወሰዱ ቁልፍ ትምህርቶች
የደቡብ ኮሪያና የኖርዌይ ተሞክሮ የሚያሳየው የአርትዖት ነጻነትን ከገንዘብ ጣልቃ ገብነት በመለየትና የምርመራ ጋዜጠኝነትን በመጠበቅ፣ ሚዲያውን የሕዝብ ጠባቂ ማድረግ እንደሚቻል ነው። በአንጻሩ የቬንዙዌላ፣ የሃንጋሪና የቡልጋሪያ ልምድ የገንዘብ በጀት ለታማኝ ሚዲያዎች ሲመደብና ሚዲያው በባለሀብቶችና በፖለቲካ ቡድኖች ሲያዝ የሙስና ቁጥጥር ፈርሶ አገራዊ አመኔታ እንደሚወድም ያስረዳል። ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ዋና ማንቂያ ደግሞ በገጽታ ግንባታ በጀትና በአበል የሚመራ የሚዲያ አሠራር ካልተገታ፣ ሚዲያው የስብዕና ገንቢና የሙስና ከለላ ሆኖ በመቀጠል ብሔራዊ ደኅንነትንና አገራዊ መረጋጋትን አደጋ ላይ መጣሉ የማይቀር መሆኑን ነው። እየታየ ያለውም ይህ እውነት ነው። በርካታ ምሳሌዎች ማንሳት፣ ስም ጠርቶ የዚህን ሰፈር ተዋናዮች፣ በየቢሮው እና በሀብታሞች ጉያ የተሰገሰጉትን በስም ማንሳት ይቻላል።
በዘርፉ የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮችና አገራዊ አንድምታቸው
በጥቅማ ጥቅም የተተበተበ የዜና አሠራርና የሙስና ተጋላጭነት ጋዜጠኝነት ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ በሚሆንበት ወቅት፣ ሙስናን የመታገል አቅሙ ሙሉ በሙሉ ይዳከማል። በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ላይ የሚታዩት ዋና ዋና ችግሮች፦
የአበልና የሪሰፕሽን ድለላ (Brown Envelope Journalism): አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የሁነት (Event) አዘጋጆች ለጋዜጠኞች አበልና ጥቅማ ጥቅም የሚሰጡት ዘገባው ተሠርቶ ሊንኩ ከተላከላቸው በኋላ መሆኑ እየተለመደ መጥቷል። ይህ አሠራር ጋዜጠኛው ጉዳዩን በሒሳዊ ዓይን እንዳይመለከትና የአዘጋጆቹን ፍላጎት ብቻ እንዲያስተጋባ ያስገድደዋል።
የገጽታ ግንባታ ንግድ (Paid PR): ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች የግል ስማቸውንና ዝናቸውን ለመገንባት በጀት በመመደብ በማኅበራዊ ሚዲያና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን የተቀነባበረ የገጽታ ግንባታ ያሠራሉ። ይህም የሕዝብን እውነት የማወቅ መብት በመጋረድ፣ በተቋማት ውስጥ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት እንዳይጋለጡ ከለላ ይሆናል።
- የሚዲያው ፖለቲካዊና የውጭ ኃይሎች ጥገኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሙያዊ ገለልተኝነትን የተላበሰ ጠንካራ ሚዲያ አለ ለማለት በማይቻልበት ደረጃ፣ ምኅዳሩ በተለያዩ ፍላጎቶች ተከፋፍሏል፦
የውስጥ ፖለቲካዊ ጽንፎች: አብዛኛው ሚዲያ የመንግሥትን አቋም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚያራምድ ወይም የተቃዋሚ ኃይሎችን ፖለቲካዊ አጀንዳ ብቻ የሚያስተጋባ ሆኗል።
የውጭ አገራት ጥቅም አስፈጻሚነት: አንዳንድ የሚዲያ አውታሮች ከውጭ ኃይሎች በሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍና ስምሪት ምክንያት የአገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዱ አጀንዳዎችን ሲያራምዱ ይስተዋላል።
የባለሀብቶችና ባለሥልጣናት ጠባቂነት: ሚዲያው የሕዝብን ብሶት ከማሰማት ይልቅ የጥቂት ባለሀብቶችን የንግድ ፍላጎትና የባለሥልጣናትን ሥልጣን የመጠበቅ ሚና ተላብሷል። «ሥልጣን አስከልካይ» የሚባሉ አሉ።
- በብሔራዊ ጥቅምና በአገር ደኅንነት ላይ የተጋረጠው አደጋ ከላይ የተጠቀሱት የጥቅም ግጭቶችና የሙያ ሥነ-ምግባር መጣሶች ተደማምረው አገርን ወደ ከፋ አደጋ እየነዱ ይገኛሉ፦
- የብሔራዊ አጀንዳ መደብዘዝ: እውነተኛ አገራዊና ብሔራዊ ጥቅሞች ከግለሰቦች የገጽታ ግንባታ፣ ከቡድኖች ፖለቲካዊ ፍላጎትና ከውጭ ኃይሎች አጀንዳ ጋር ተቀላቅለው ሕዝቡ እውነቱን ከሐሰት እንዳይለይ አድርገውታል።
- የተጠያቂነት መጥፋት: ጋዜጠኛው በአበልና በጥቅማ ጥቅም አፉ በመያዙ፣ በአገር ሀብት ላይ የሚፈጸም ዝርፊያና የአስተዳደር በደል ተጋልጦ እርምት እንዳይወሰድበት እንቅፋት ሆኗል።
- የሕዝብ አመኔታ መሸርሸር: ዜጎች በአገር ውስጥ ሚዲያዎች ላይ ያላቸው እምነት በመጥፋቱ፣ መረጃ ለማግኘት ወደ ያልተረጋገጡ ወሬዎችና አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች እንዲያዘነብሉ በር ከፍቷል።
የመፍትሔ ሐሳቦች
ከላይ የተዳሰሱትን የጥቅም ግጭቶች፣ የአበል ድለላና የብሔራዊ አጀንዳ መደብዘዝ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚከተሉት የተቀናጁ እርምጃዎች ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርና የአርትዖት መርሆች ከአበልና ከጥቅማ ጥቅም ነጻ መሆን (Zero-Tolerance for Per Diem & Kickbacks): ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከግል ድርጅቶች ወይም ከሁነት አዘጋጆች ዘገባ በመሥራት ወይም ሊንክ በመላክ ብቻ የሚከፈል ማንኛውንም አበል፣ ስጦታ ወይም የጉዞ ወጪ መቀበል ሙሉ በሙሉ ማቆም አለባቸው። ለሥራ የሚያስፈልጉ ወጪዎች በራሱ በሚዲያ ተቋሙ መሸፈን ይኖርባቸዋል።
ዜናን ከማስታወቂያና ከሕዝብ ግንኙነት (PR) መለየት: የሚከፈልባቸው የገጽታ ግንባታ ሥራዎች፣ ስፖንሰር የተደረጉ ይዘቶችና የሕዝብ ግንኙነት መግለጫዎች በግልጽ እንደ «ማስታወቂያ» ወይም «የተከፈለበት ይዘት» (Sponsored / Paid Content) መለያ ሊሰጣቸው ይገባል። በዜና ቅርጽ የሚቀርቡ ዘገባዎች በገለልተኛ ማረጋገጫና በበርካታ ምንጮች ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው።
የምንጭ ማጣራትና የብሔራዊ ጥቅም ሚዛን: ዘገባዎችን ከማተም በፊት ከዋና ምንጮች ማረጋገጥ፣ የመጀመሪያ መረጃ አመንጪዎችን በትክክል መጥቀስ እና ጊዜያዊ የፖለቲካ ወይም የገንዘብ ፍላጎቶችን ከረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅምና የሕዝብ ደኅንነት በማስቀደም መሥራት ያስፈልጋል።
የጥቅም ግጭት ይፋ ማድረግ: አንድ ጋዜጠኛ ወይም ሪፖርተር ከዘገባው ርዕሰ ጉዳይ ጋር የግል፣ የቤተሰብ ወይም የፋይናንስ ግንኙነት ካለው፣ ጉዳዩን በአርትዖት ደረጃ አስቀድሞ ማሳወቅና ከዘገባው መራቅ ይኖርበታል።
የሚዲያ ተቋማት የአሠራርና የፋይናንስ ማሻሻያዎች
የገቢ ምንጮችን ማብዛትና ግልጽ ማድረግ: ሚዲያዎች በአንድ ወገን የመንግሥት በጀት፣ በአንድ ባለሀብት ወይም በውጭ ድጋፍ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆኑ የንባብ/የተመልካች ድጋፍ፣ ግልጽ የንግድ ማስታወቂያ እና ሌሎች ዘላቂ የገቢ ሞዴሎችን ማጎልበት አለባቸው። የሚዲያ ባለቤትነትና የገንዘብ ምንጮች ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለባቸው።
የአርትዖት ነጻነትን ማረጋገጥ: የአርትዖት ክፍል (Editorial) ከሽያጭ፣ ከማስታወቂያና ከአስተዳደር ክፍሎች ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ እንዲሠራ የሚያስችል ግልጽ የውስጥ መመሪያ መኖር አለበት። ጋዜጠኞች ያለ ስጋት የምርመራ ዘገባ እንዲሠሩ የደመወዝና የሥራ ዋስትና መሻሻል አለበት።
የውስጥ ሥነ-ምግባር ኮሚቴ ማቋቋም: እያንዳንዱ የሚዲያ ተቋም የሥነ-ምግባር ጥሰቶችንና የጥቅም ግጭት ቅሬታዎችን የሚመረምር የውስጥ አሠራር በመዘርጋት ተጠያቂነትን ማስፈን ይኖርበታል።
የፖሊሲ፣ የሕግና የሙያ ማኅበራት እርምጃዎች
ራስን በራስ የመቆጣጠር ሥርዓትን ማጠናከር: በመንግሥት ቀጥተኛ ቁጥጥር ፈንታ፣ በራሳቸው በጋዜጠኞችና በሚዲያ ተቋማት የሚመራ ጠንካራ የሙያ ምክር ቤት (Press/Media Council) ወይም የሥነ-ምግባር ኮሚሽን አቅም ማጎልበት እና የቅሬታ አፈታት ሥርዓትን ማዘመን ያስፈልጋል።
የመረጃ ነጻነትና የሙስና መከላከል አሠራርን ማቀናጀት: የመንግሥት ተቋማት መረጃን በግልጽነትና በወቅቱ የመስጠት ግዴታቸውን እንዲወጡ ማድረግ፣ እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነት በጀቶች ለሚዲያ ድለላ ሳይሆን ለሕዝብ ግልጽ መረጃ ተደራሽነት እንዲውሉ የቁጥጥር ማዕቀፍ ማበጀት።
የሚዲያና የመረጃ ዕውቀትን (Media Literacy) ማስፋፋት: ሕዝቡ የተቀነባበሩ የገጽታ ግንባታ ዘመቻዎችን፣ የሐሰት መረጃዎችንና ፕሮፓጋንዳን ከተረጋገጠ ጋዜጠኝነት እንዲለይ በትምህርትና በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መደገፍ።
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳር አገርን ከአደጋ ለመታደግና ሙስናን በብቃት ለመታገል እንዲችል፣ በቅድሚያ ራሱን ከጥቅም ግጭት፣ ከገንዘብ ድለላና ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ማጽዳት ይኖርበታል። የጋዜጠኞች የግል ሥነ-ምግባር መታነጽ፣ የተቋማት የፋይናንስና የአርትዖት ነጻነት መረጋገጥ እንዲሁም ጠንካራ የሙያና የፖሊሲ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት የሕዝብን ድምፅ ለማስከበርና ብሔራዊ ደኅንነትን ለመጠበቅ የማይታለፉ ቁልፍ እርምጃዎች ናቸው።
ዝግጅት ክፍሉ / ይህ ጽሁፍ የትኛውንም ሚዲያ ወይም የሚዲያ ተቋም አባላት ታሳቢ አድርጎ የተሰራ አይደለም። ዓላማው የሚመለከተው የመንግስት አካላ እንዲያስብበት ለማድረግ ሲሆን፣ በቀጣይ ለውጥ አልባ ስለሆነው የኮሙኒኬሽን ችግርና ክፍተቱ ያስከተለውን ጣጣ እነዲሁም ለምን ለውጥ እንዲደረግበት እንደማይፈለግ የሚጠይቅ ጸሁፍ እናቀርባለን።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






