አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | ኢትዮጵያ ከአባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር ያላት መልክዓ ምድራዊና ታሪካዊ ትስስር በፖለቲካዊ ትርክቶች፣ በማስገደድ እርምጃዎች ወይም በማተራመስ ድርጊቶች ሊቀየር እንደማይችል አስታወቀች።
የኢትዮጵያ አቋም ይፋ የሆነው ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ አጠቃቀምና በቀይ ባሕር ጉዳይ የጋራ መግለጫ ካወጡ በኋላ ነው። አራቱ አገራት ኤል አላሚን ስምምነት በሚል በገለጹት መግለጫ ላይ፣ ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም አንጻር ግብፅና ሱዳንን ሊጎዳ የሚችል ተናጠል እርምጃን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል። በተጨማሪም የቀይ ባሕር አስተዳደርና ቁጥጥር በባሕሩ ዳርቻ ባላቸው አገራት ኃላፊነት ሥር እንደሚወድቅ አስታውቀዋል።
ምንም እንኳን የአራቱ አገራት መግለጫ የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚመለከት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ስም በመግለጫው ላይ በቀጥታ አልተጠቀሰም።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አራቱን አገራት ወይም ያወጡትን መግለጫ በቀጥታ ሳይጠቅስ ባወጣው አጸፋዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ መነሻ እንደሆነች እና ወንዙ ለናይል የውኃ ፍሰት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚያበረክት አስታውሷል። በጥናት በተረጋገጠው መሰረት ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ 85 መቶኛው ከከርሷ የሚወጣ ነው።
በመሆኑም በአባይ ወንዝ አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ የሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶች ይህንን መሠረታዊ መልክዓ ምድራዊ እውነታ ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
ይህ አቋም በአባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየውን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ክርክር ያሳያል። ኢትዮጵያ በበኩሏ የውኃ ሀብቷን ለልማት የመጠቀም መብቷ እንዲከበር ስትጠይቅ ግብፅ ደግሞ በአባይ ላይ ያላትን የታሪክ እና የውኃ ደህንነት ጥቅም ትጠቅሳለች።
የቀይ ባሕር ጉዳይ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴ ባወጣው ጠንካራ መግለጫ ከአባይ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን መልክዓ ምድራዊና ታሪካዊ ትስስር አጽንዖት ሰጥቶ ገልጿል።
የፖለቲካ ድንበሮች በጊዜ ሂደት ሊቀያየሩ ቢችሉም፣ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ጥብቅ ትስስር እንደቀጠለ ሚኒስቴሩ ገልጿል። በመግለጫው መሠረትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ዳርቻ የምትርቀው በ48 ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ እንደሆነም አመልክቷል።
ስለሆነም በቀጣናዊ የባሕር ጉዳዮችና በደኅንነት መዋቅር ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅሞች እና ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ዘላቂ ትስስር ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።
“እውነታዎች በፖለቲካ ትርክት አይቀየሩም”
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ከተጠቀመባቸው ጠንካራ አገላለጾች መካከል፣ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊና ታሪካዊ እውነታዎች በፖለቲካዊ ትርክቶች፣ በማስገደድ እርምጃዎች ወይም በማተራመስ ድርጊቶች ሊቀየሩ እንደማይችሉ ያስገነዘበበት አግባብ ነው።
ሚኒስቴሩ በተጨማሪ፣ “በተላላኪዎች አማካይነት የሚወሰዱ እርምጃዎች ወይም የጥቃት ድርጊቶች” በመሬት ላይ ያለውን እውነታ እንደማይቀይሩም አመልክቷል። እንደ ሚኒስቴሩ አቋም፣ እነዚህ ድርጊቶች ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን “ሕጋዊ ጥቅም፣ ሚና እና ኃላፊነት” ሊያሳንሱ አይችሉም።
ኢትዮጵያ ለውይይት በሩን ክፍት አድርጋለች
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላማዊ ግንኙነትን፣ የጋራ መከባበርን እና ትብብርን ማጠናከር እንደምትቀጥል ገልጻለች። በተመሳሳይ ሉዓላዊነቷን፣ የግዛት አንድነቷን እና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች። ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመታቸውን ከተረከቡ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር የመጓዟ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን ሲያስታውቁ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ እንደምታምን፣ ነገር ግን ሴራዎችንና ያለተገቡ አካሄዶችን በድል እንደምትወጣ አስታውቀዋል።
ሚኒስቴሩ የቀጣናው አገራት የጋራ ፈተናዎችን በግጭት ሳይሆን በውይይት እና በትብብር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። የአባይ ውኃ አጠቃቀም፣ የቀይ ባሕር መዳረሻ እና የቀጣናው ደኅንነት ጉዳዮች በአንድ የክልላዊ ፖለቲካ አውድ ውስጥ እየተገናኙ በመምጣታቸው፣ የሚቀጥለው የዲፕሎማሲ ውይይት በእነዚህ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ይሆናል፤
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






