አዲስ ሪፖርተር ዜና — “አስደንጋጭ ነበር” በማለት የጋራ መድረኩን መረጃ ለአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግተን ተባባሪ ያካፈሉ፣ እንዳሉት ሕወሓት ለሻዕቢያ አሳልፎ የሰጣቸው የሠራዊት አመራሮችና ባለሥልጣኖች እንዲረሸኑ ተወስኗል። እስካሁን ግን ተግባራዊ አልሆነም።
ይህ የተሰማው ባለፈው ረቡዕ አቶ ልደቱ አያሌውና አቶ ነዓምን ዘለቀ በጋራ ተቀናጅተው በመሠረቱት የሕዝባዊ እምቢተኛነት አመቻች የጋራ መድረክ መደበኛ ስብሰባ ሲሆን፣ ስብሰባው ለስድስተኛ ጊዜ አባላቱ ባለመገኘታቸው ለዕሁድ በተባለበት ወቅት ነው።
ዘወትር እንደሚደረገው አባላት እስኪሰባሰቡ በሚደረገው መረጃ የመቀያየር ልምድ፣ በጋራ መድረኩ የሕወሓት ተወካይና የፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ወኪል የሆኑት አቶ አባይ ግደይ “አስደንጋጭ” የተባለ መረጃ ይፋ አድርገዋል።
በስብሰባው የኦሮሞ ወኪል አድርገው ራሳቸውን የሚጠሩ፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ወኪል፣ የጋምቤላ፣ ወዘተ. በተደጋጋሚ ሊገኙ ባለመቻላቸው ቅሬታ ከተሰማ በኋላ አቶ አባይ “ጄኔራሎችና የሚፈለጉ ሹማምንቶች ለሻዕቢያ ተላልፈው ተሰጥተዋል” አሉ።
ዜናውን ከተሳታፊዎች ሰምተው የተናገሩ እንዳሉት አቶ አባይ፣ ከብልጽግና ጋር እንደሚሠሩ የተደረሰባቸው ሦስት ከፍተኛ የሠራዊት አዛዦች እና የፖለቲካ ሹመኞች ለሻዕቢያ ተላልፈው ተሰጥተዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ንዴት እና እልህ የተቀላቀለበት መረጃ ሲሰጡ ነበር” በማለት የሰሙትን በዝርዝር ያስረዱት የዜናው ባለቤቶች፣ አቶ አባይ ለሻዕቢያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ይፋ ከማድረግ ውጪ ስም አልዘረዘሩም። ይሁን እንጂ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደን በማንሳት “ሁሉም ከእነ ጻድቃንና ጌታቸው ረዳ ጋር ሲሠሩ የነበሩ ባንዳዎች ነበሩ” በማለት ከሰዋል።
ከስብሰባው በኋላ “እነዚህ ሰዎች ለሻዕቢያ ከተሰጡ እጣ ፋንታቸው እንደ እነ አቶ ስዩም መስፍን፣ አባይ ጸሃዬ፣ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ ወዘተ. ይረሸኗቸዋል” በማለት በሰሙት አዝነው የተነጋገሩ፣ ይህንኑ በማንሳት ከሻዕቢያ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው ጥያቄ እንዳቀረቡ አመልክተዋል።
“ባንዳ ከሆኑ አይቀርላቸውም” በማለት መልስ እንደተሰጣቸው ያመለከቱት እነዚሁ ወገኖች፣ የሰዎቹ መታሰር በሕወሓት የውጭ አመራሮች ዘንድ መለያየት መፍጠሩና ሕይወታቸው ላይ አንዳችም አደጋ እንዳይደርስ የጠየቁ መኖራቸው ታውቋል። ይህንን አስመልክቶ ጥያቄ ለመሰንዘር ተባባሪያችን የጋራ መድረኩ የሻዕቢያ ወኪል ለሆኑት አቶ ነዓምን በግል ስልካቸው ቢደውልላቸውም ስልካቸውን ባለመመለሳቸው ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልተቻለም። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስልክ ካነሱና ጥያቄውን ከሰሙ በኋላ ተሳድበው ስልክ ዘግተዋል።
በተመሳሳይ ዜና የሻዕቢያና የሕወሓት ጥምረት ሲያሸንፍ የትግራይ ሰላም ኃይሎች አመራሮች ሙሉ በሙሉ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው፣ በስምና በደረጃ ተመዝግበው የተያዙ እንዳሉ ተባባሪያችን ከዋሽንግተን ዘግቧል።
ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ከወዲሁ የሞት ቅጣት የተወሰነባቸው እንደሆነ የመረጃ ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበው ተባባሪያችን፣ ከአገር መከላከያ ውስጥም በየደረጃው ተለይተው እንዲረሸኑ የተወሰነባቸው ቁጥራቸው በርካታ እንደሆነና ውሳኔው በሻዕቢያ አቅራቢነት የሚሰላ እንደሆነ አመልክቷል።
ከላይ የተጠቀሱት የሕወሓት የወቅቱ ከፍተኛ አመራሮች በሻዕቢያ ተይዘው ሲገደሉ የአገር መከላከያ እጅ የወደቁት በቃሬዛ እና በድጋፍ ከምሽግና ከየውሻ ተፈልገው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ያስታወሱ፣ አሁን በሻዕቢያ እጅ የወደቁ የሕወሓት አመራሮችና የሠራዊት አዛዦች እጣ ፈንታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ አመልክተዋል። ሚዲያዎች፣ በተለይም የሕወሓት ደጋፊዎች ከወዲሁ ጫና እንዲፈጥሩ አመልክተዋል።
ሌላው አቶ አባይ ያስታወቁት፣ አሁን ላይ ሠራዊታቸው ያፈገፈገው ሆን ብሎ በአፋር ክልል ኃይል በማጠናከር ሰመራን ተቆጣጥሮ የኤ-አንድና ኤ-ሁለት የጅቡቲን መስመር ለመቁረጥ ታስቦ ነው።
ሻዕቢያ ጽምዶን ለማቋቋም ዋና መነሻ የሆነው በአሰብ በኩል ያለውን ስጋት ለመከላከል በአፋር በኩል ሰፊ የጦርነት ቀጠና በመዘርጋት የኢትዮ-ጅቡቲን መስመር በመቁረጥ መንግሥት ለማፍረስ አቅዶ እንደሆነ ማስረጃ አቅርበን አስቀድመን መዘገባችን አይዘነጋም።
ሰሞኑን ይፋ በሆኑ መረጃዎች፣ የዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች እንደዘገቡት፣ የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት ሃጂ አወል ይፋ እንዳደረጉት፣ እንዲሁም በጦርነት የተማረኩና የተገደሉ የሻዕቢያ ወታደሮች ሰነድ መረጃ ሆኖ እንዳሳየው ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ በይፋ ውጊያ አውጀዋል።
በስብሰባው ላይ አቶ አባይ በወልቃይት፣ በራያ፣ ሰቆጣ፣ ቆቦ፣ አላማጣ ግንባሮች ሕወሓት ጦርነት የጀመረው ለማዘናጊያ እንደሆነ አመልክተው፣ የጅቡቲን መስመር መቁረጥ ከሻዕቢያ ጋር የተደረሰ ቁልፍ ስምምነት እንደሆነ ማረጋገጫ መስጠታቸው እውነታውን ያጠናክረው ካልሆነ አዲስ ጉዳይ እንዳልሆነ መረጃውን የሰጡ አመልክተዋል።
እነዚህ ወገኖች መንግሥት በይፋ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሻዕቢያና ግብጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚችሉትን ሁሉ ኃይል ሰብስበው መነሳታቸውን በግልጽ ማሳወቅና ሕዝብ አገሩን ከመከላከያና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን እንዲከላከል፣ በያለበት ዘብ እንዲሆን ጥሪ ማድረግ እንዳለበት አስታውቀዋል። ሚዲያዎችም ሕዝቡን በይፋ ከብሔራዊ ጥቅምና አደጋ አንጻር ሐቁን ሊያስታጥቁ እንደሚገባ መክረዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






