አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሱዳንን ጦርነት ለማስቆምና ሁሉንም ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ሲቪል ኃይሎች ያሳተፈ አገራዊ ውይይት ለማካሄድ ያቀረቡት ጥሪ የተለያየ ምላሽ እያገኘ ሲሆን፣ ከRSF ጋር የተያያዘው የታሲስ ጥምረትና የሲቪል ፖለቲካዊ ኃይሉ ሱሙድ ተነሳሽነቱን በደስታ ተቀብለውታል፤ በተቃራኒው በጄኔራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን መንግሥት ኢትዮጵያ ገለልተኛ አስታራቂ ልትሆን አትችልም በሚል ጥሪውን ውድቅ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሁሉም የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችና የፖለቲካ አካላት ለሰላም ንግግር ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ያቀረቡት ግልጽ ደብዳቤ፣ በሱዳን አስከፊ ጦርነት ዙሪያ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ምኅዳር በአዲስ መልክ አነቃቅቶታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥታ ለሱዳን ሕዝብ ጥሪ ማቅረባቸው በጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ወታደራዊ መንግሥት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ሽብልቅ ሆኖ አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተታቸው እየተነገረ ነው።
በዓረብኛ ቋንቋ ተጽፎ ለሱዳን ሕዝብ የቀረበው ይህ ደብዳቤ፣ የሁለቱን ሕዝብ የቆየ ታሪካዊ ትሥሥር እንዲሁም “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚለውን መርህ አጉልቶ አሳይቷል። እዚህ ላይ ትልቁ ነጥብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ራሳቸውን የንግግሩ አሸማጋይ አድርገው አለማቅረባቸው ነው። ይልቁንም የኢትዮጵያ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን እንደ ገለልተኛ የመወያያ መድረክ አድርገው አቅርበዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማዕከል እንደመሆኗ፣ ተፋላሚ ጄኔራሎችን፣ ሲቪል ፖለቲከኞችንና የማኅበረሰብ ተወካዮችን በአንድ ጣራ ሥር ለማሰባሰብ የሚያስችል የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ አቅም አላት።
ከሱዳን ወገን የተሰጠው ምላሽ ፈጣንና ብዙ ነገር የሚናገር ነበር። የሰላም ደብዳቤውን ያልተጻፈ ሐሳብ ከጅምሩ ግብ እንደመታ በሚገልጽ መልኩ በፖርት ሱዳን የመሸገው የጄኔራል አልቡርሃን አስተዳደር ግብዣውን በችኮላ ገፍቶታል፤ ውድቅ አድርጎታል። በአንጻሩ ግን በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የሲቪል ጥምረት “ሶሙድ”ን ጨምሮ ዋና ዋና የሲቪል አመራሮች፣ ጥሪውን ደም መፋሰሱን ለማስቆም የተገኘ እውነተኛ ዕድል ነው ሲሉ በደስታ ተቀብለውታል።
ሃምዶክና የሚመሩት የሶሙድ ጥምረት በምዕራባውያን ሀገራት ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነትና ተጽዕኖ ያላቸው በመሆኑ፣ ዲፕሎማሲያዊ ሐሳቦችን ወደ ተጨባጭ ተግባር የመቀየር ትልቅ አቅም አላቸው። በተመሳሳይ መልኩ ከፈጥኖ ደራሽ ሰጪ ኃይሎች (RSF) ጋር ግንኙነት ያላቸው ተወካዮችም በመድረኩ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ በሱዳን ወገኖች መካከል የተፈጠረው የአቋም ልዩነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እርምጃ ብልሃት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ባለፉት ወራት የፖርት ሱዳን አስተዳደር በጄኔቫ የተደረጉትን ጨምሮ በዋና ዋና የተኩስ አቁም ድርድሮች ላይ ላለመገኘት ያሳየው ግትርነት፣ ምዕራባውያን መንግሥታትን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና የአፍሪካ ኅብረትን ክፉኛ አስቆጥቷል። ረሃብ እየተስፋፋና ከተሞች እየወደሙ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ንግግር እንዲደረግ የቀረበውን የጎረቤት ሀገር መሪ ጥሪ መግፋት፣ አልቡርሃን ጦርነቱ እንዲቆም አይፈልጉም ብሎ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያምን ያደርጋል የሚለው ካሁኑ እየተወራ ያለ ጉዳይ ሆኗል።
ለኢትዮጵያም ቢሆን ይህንን የሰላም እርምጃ መውሰድ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ጦርነቱ በኢትዮጵያ ምዕራባዊ ድንበርና ወሳኝ ሀገራዊ መሠረተ ልማቶች አቅራቢያ ወደምትገኘው የሱዳን ብሉ ናይል ግዛት እየተጠጋ ከመምጣቱ አንጻር ለኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው።
ባለፉት ወራት የዲፕሎማቶች መባረርና ከፖርት ሱዳን በኩል የሚሰነዘሩ ከባድ ውንጀላዎች ቢኖሩም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውጥረቱ እንዲባባስ ከመተው ይልቅ የሰላም እጃቸውን ዘርግተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላም ያላትን ታሪካዊ ሚና ዳግም አረጋግጠዋል። አዲስ አበባ እ.ኤ.አ. በ2019 የሱዳንን የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት በስኬት ማስተናገዷ የሚታወስ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ከተማዋ ያንን ታሪክ ትደግመዋለች የሚል እምነት አላቸው።
ሁሉንም ወገኖች ወደ አንድ የድርድር ጠረጴዛ ማምጣት ቀላል አይሆንም። በሱዳን ጦር ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች፣ ላለፉት ወራት ሲነዙ በቆዩ መራራ ቅስቀሳዎችና የድንበር ጣልቃ ገብነት ክሶች ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ያለው ጥርጣሬ አሁንም ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል ምዕራባውያን ዲፕሎማቶችና ቀጠናዊ ተቋማት ትኩረታቸውን በተባበሩት መንግሥታት፣ በአፍሪካ ኅብረትና በጎረቤት ሀገራት በተጀመሩት ነባር የሽምግልና መድረኮች ላይ አድርገዋል።
ያም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የዲፕሎማሲ አጀንዳ ቀይረውታል። ዓለም አቀፍና ቀጠናዊ አሸማጋዮች ሥራቸውን የሚያከናውኑበትን የአዲስ አበባን በር ክፍት በማድረግ፣ የሱዳን ቀውስ በመሣሪያ እንደማይፈታና ለንግግር ጀርባቸውን የሚሰጡ አካላት ለብቻቸው ተነጥለው እንደሚቀሩ ለቀጠናውና ለመላው ዓለም ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተለይ የአልቡርሃን ወታደራዊ አገዛዝ የትህነግ ገዳይ ቅጥረኞች ወታደራዊ ሥልጠና እንዲያደርጉ፤ በሱዳን በኩል ሆነው ኢትዮጵያን እንዲወጉ፤ በሱዳን በኩል ለትህነግ፣ ለፋኖ እና ለሽኔ ታጣቂዎች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች (ድሮንንም ጨምሮ) ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በማድረጉ በማስረጃ የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ ከኢትዮጵያ በኩል እንዲህ ዓይነት የሰላም ጥሪ መቅረቡ ግብፅ ያሳሰበ፣ ሻዕቢያን ያስጨነቀ፣ አልቡርሃንን ደግሞ በዲፕሎማቲክ ሽብልቅ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ሆኗል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






