አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ | ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀገራቸው ከኤርትራ ጋር ስላላት ግንኙነት፣ ስለ ባሕር በር ተደራሽነት ጥያቄ፣ እንዲሁም ስለ ቀጣናው ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም የሚያብራራ መልዕክት አስተላለፉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው «ኢትዮጵያ በሰማይም፣ በምድርም ታፍና ከምትኖር…» በማለት የኤርትራን አገዛዝ ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ ለኤርትራና ለሌሎች አገራት በመላላክ ጠብ መንጃ ያነሱ አካላትን ልክ «ፓራሹት ከሰማይ ሲወርድ ዘላዩ አጥብቆ እንደሚይዘው፣ መሬት ሲያርፍ ወዲያው እንደሚወረውረው» መስለው፣ «ነገ ከመወርወራችሁ በፊት አገራችሁን ከመጉዳት ተቆጠቡ» ሲሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያን በአየርም በምድርም ለማፈን የሚያስቡ እና እየተዘጋጁ ያሉትን ቡድኖችና አገራት “አይሳካላቹህም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይህቺ ባቄላ ካደረች” በሚል የኢትዮጲያን እደገት ፍርሃቻ እንቅልፍ ነስቷቸው እዛም እዚህም እሳት ለመለኮስ ለሚሯሯጡት፣ “ኢትዮጵያ አድራለች፤ ከርማለች ተዋት” በማለት ተስፋ እንዲቆርጡ አሳስበዋቸዋል። የሚጠቅመው ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የኤርትራ ግንኙነትና ዋና ጥያቄዎች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኤርትራ ጋር ስላለው ግንኙነት በተለየ መልኩ ባነሱት ሐሳብ፣ ለኤርትራ መንግሥት ሁለት ዋና ዋና ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ገልጸዋል። የመጀመሪያው ጥያቄ የኢትዮጵያን ጠላቶች መደገፍና ማስጠለል ማቆም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ የልማት ትብብር ላይ መሥራት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግጭት ይልቅ ሰላማዊ ውይይት ሁሌም ተመራጭ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የቀይ ባሕር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ
የቀይ ባሕርን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በተመለከተ ባነሱት ሐሳብ፣ የኢትዮጵያ መረጋጋት ለመላው ቀጣና ሰላምና ደኅንነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። በታሪክ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ሲቀያየሩ እንደነበረው ሁሉ፣የቀይ ባሕር የአሁኑ የንግድ መተላለፊያ የበላይነት ወደፊት ሊለወጥ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምትከተለው አካሄድ ፍጹም ዲፕሎማሲያዊ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም በጆርዳን እና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የተደረጉ ስምምነቶችን እንዲሁም ለኢራቅ የተሰጠውን የባሕር በር ዕድል በታሪካዊ ምሳሌነት አንስተዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትሻው በወረራ ወይም በኃይል ሳይሆን በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ቀጣናዊ ትብብር፣ የውጭ ኃይሎች ጥገኝነትና የሀገር ውስጥ ሰላም
በተጨማሪም የቀጣናው ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና በሌሎች ኪሳራ ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን አስገንዝበዋል። ሀገራት ለደኅንነታቸው ሲሉ በውጭ ኃይሎች ላይ መተማመን እንደሌለባቸው በማስጠንቀቅ፣ ግጭት በሚከሰትበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ የውጭ ድጋፍ ብዙውን ጊዜ እንደሚከስም ተናግረዋል። ዋናው ጉዳይ ሲሆን እንደሚሸሹ “በትግራይ ደሮን እንተኩሳለን ብለው የመጡ ‘አስወጡን’ በማለት ሸሽተዋል” በማለት እንደማያዋጡዋቸው አስታውቀዋል።
በሀገር ውስጥ ሰላምና አንድነት ዙሪያም መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት እንዲመጡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደ ስኬት በማንሳት ጥሪ አቅርበዋል። በሀገር ውስጥ ያለውን ግጭት የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም የራሱን አካል እንደሚያጠቃበት ሕመም መስለው የገለጹ ሲሆን፣ በብሔርና በሃይማኖት የሚደረጉ ከፋፋይ ቅስቀሳዎችን እና የውጭ ተላላኪነትንም ነቅፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ መንግሥታቸው በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመና የተረጋጋ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ወንድማማችነትን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንና ማንኛውም የወደብ ተደራሽነት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ብቻ መያዝ እንዳለበት በድጋሚ አስምረውበታል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






