አዲስ ሪፖርተር – የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት (EuroCham) የአውሮፓ ህብረት የአዲሱ የደን መጨፍጨፍ መቆጣጠሪያ ደንብ (EUDR) የተፈፃሚነት ጊዜ እንዲራዘም የቀረበውን ሀሳብ የሚደግፍ ቢሆንም፣ ይህ ደንብ በታህሳስ 30 ቀን 2025 ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የኢትዮጵያን አነስተኛ አርሶ አደር ላይ የተመሰረተ የቡና አምራች ሞዴል የሚያንፀባርቁ ተግባራዊ መፍትሄዎች እንዲፈለጉ አጽንኦት ሰጥቷል።
የደን መጨፍጨፍን የመከላከል ደንቡ ዓላማ የሚደገፍ ቢሆንም፣ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት የቡና ዘርፉን በቦታው ላይ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለማሳየት ከመከስከረም 21 እስከ መስከረም 22 ድረስ ወደ ጂማ እና ከፋ የቡና አብቃይ አካባቢዎች የአውሮፓ ህብረት ልዑካንን መርቶ ይዞ ሄዶ ነበር። ልዑኩ የኢትዮጵያ ቡና ወደ አውሮፓ የሚላከው የቡና ንግድ 35% የሚሆነውን እንደሚሸፍን እና ከአምስት ሚሊዮን በላይ አነስተኛ አርሶ አደሮችን እንደሚደግፍ ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ የቡና ምርት ሥርዓት በአነስተኛ አርሶ አደሮች የሚመራ፣ ከደን የተዋሃደ (forest-integrated) እና በእርሻ ደን (agro-forestry) የምርት ሥርዓቶች ስር የሚካሄድ ነው። ይህ ሞዴል በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በደንብ የተጠበቀ የአካባቢ ጥበቃ ዘላቂነት ምሳሌ በመሆን፣ የብዝሃ ሕይወትን በመጠበቅ በኢትዮጵያ ደኖችን የሚያጠፋ ሳይሆን የሥነ-ምህዳሮች ጠባቂ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ ጉብኝት ወቅት ተሳታፊዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሽ ዋገሾ ሰብሳቢነት በተደረገ የውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ቡና “የደን መጨፍጨፍ ምክንያት ሳይሆን የሥርዓተ-ምህዳር ጠባቂ” መሆኑንና ለትውልዶች ሲካሄድ የቆየ ዘላቂ የአምራች ሞዴል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ከተነሱት ዋና ዋና ስጋቶች አንዱ የጂኦ-ሎኬሽን መረጃን ለመሰብሰብ አስፈላጊ የሆኑ ዲጂታል መሳሪያዎች እና ፋይናንስ በአብዛኞቹ አነስተኛ አርሶ አደሮች ዘንድ አለመኖሩ ሲሆን፣ ይህም የEUDRን የክትትል መስፈርት(Traceability) ለማሟላት ከፍተኛ ወጪ እና ጊዜ እንደሚጠይቅ የኦሮሚያ ቡና አርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ዩኒየን (OCFCU) ገልጿል። ላኪዎችም የደንቡን ማስፈጸሚያ ወጪ መሸከም ካቃታቸው፣ ኢትዮጵያ ቡናዋን ወደ EU ገበያዎች ከመላክ ይልቅ ወደ ቻይና እና የባህረ ሰላጤ አገራት ወደመሳሰሉ ተለዋዋጭ ገበያዎች ልትዞር እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።
የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ቡና “የደን መጨፍጨፍ ችግር አካል ሳይሆን የመፍትሔው አካል” መሆኑን አምኗል፤ እንዲሁም የደንቡን የትግበራ ሸክም በመጨረሻ በአውሮፓ አስመጪዎች ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ገልጿል። አውሮፓውያን ገዥዎች ቡናው በበቂ ሁኔታ መከታተል ስላልተቻለ እስከ 4% የሚደርስ ቅጣት ስለሚጠብቃቸው ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ቡና መግዛታቸውን መቀነስ ጀምረዋል።
አምባሳደር ፍሮም-ኤምስበርገርም የኢትዮጵያ ቡና “ከውጪ ንግድ በላይ የባህል ቅርስ” መሆኑን እና ይህን ልዩ ዘላቂ የአምራች ሞዴል መታወቅና መጠበቅ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። በመጨረሻም EuroCham የአውሮፓ ህብረት የደንቡን የትግበራ የጊዜ ሰሌዳን እንዲያጤነው፣ የኢትዮጵያን አነስተኛ አርሶ አደር ሞዴል የሚመጥን የክትትል ስርዓት ለማበልጸግ ቴክኒካዊ እና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ እንዲሁም ዲጂታል ማረጋገጫ ማዕቀፎችን እንዲገነባ ጥሪ አቅርቧል።
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






