“ታደሰ ወረደ እንኳን ዳግም ትግራይን ሊመሩ ከሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጋር ለፍርድ መቅረብ አለባቸው” – በትግራይ ህዝብ መከራ ውስጥ እጃቸው እንዳለበት መረጃ አለ ተብሏል

Date:

ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ ስራውን በመበጣጠስ፣ በግልጽና በስውር “ጽንፈኛ” ከሚባሉት ኃይሎች ጋር ሲሰሩ የነበሩ በመሆናቸው መንግስት መለሳለሱን አቁሞ ህግ ፊት ከሚቆሙት መካከል እንዲመድባቸው ጥያቄ ቀረበ። “እሳቸው ያስተዳድሩታል” በሚባለው ሚዲያና ሌሎች የማህበራዊ አምደኞች ያስጀመሩት ዳግም ወደ ስልጣን የመመለስ እንቅስቃሴ ገደብ እንዲደረግበት ተጠየቀ።

ይህንን ያሉት ወገኖች ታደሰ ወረደ በትግራይ ህዝብ ስቃይና መከራ ውስጥ እጃቸው እንዳለበት ከበቂ በላይ ማስረጃ መኖሩን ገልጸዋል። ወደ ህግ ሲቀርቡ ከሙስና ጀምሮ አሁን ጦርነት ከቀሰቀሰው ቡድን ጋር ያላቸውን ቀጥተኛ ግንኙነት የሚያጋልጥ መረጃ እንዳላቸው የሚገልጹ “ወዲ ወረደ ስልታን የሚመኙት ከህግ ተጠያቂነት ራሳቸውን ለመከላከል እንጂ ለሌላ እንዳልሆነ እርግጠኞች ነን” ብለዋል። ጡርታቸውን አስከብረው ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲያመሩም የመከሩ አሉ።

ከመጋቢት 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የቀድሞውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን በመተካት ወንበሩን የተረከቡት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ ተቆጥሮና ተለክቶ ዲፕሎማቶች፣ ታዛቢዎችና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ በተገኙበት፣ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ቃለ መሃላ በመፈጸም ነበር።

አቶ ጌታቸው በፕሬዚዳንትነት በነበሩበት ወቅት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ታደሰ ወረደ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የትግራይ ክልል ሲዋቀር ጀምሮ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ በመሆን ለሁለት ዓመታት እንዲያገለግሉ ሲደረግ ከጅምሩ ቅሬታ ነበር።

በጦርነቱ ወቅት የትግራይ መከላከያ ኃይሎች (TDF) ዋና አዛዥ የነበሩት ታደሰ ወረደ፣ የአቶ ጌታቸው ካቢኔ ፈርሶ እሳቸው ስልጣን እንዲይዙ ሲደረግ በዋናነት የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን አጀንዳ ያስፈጸሙ እንደሆኑ በማስረጃ የሚዘረዝሩት፣ ታደሰ ወረደ በወንጀል ሊመረመሩ የሚገባቸው “ሴረኛ” እንደሆኑ በማመልከት ነው። የአቶ ጌታቸው ድክመትና ቸልተኛነት እንዳለ ሆኖ፣ ታደሰ ወረደ አስተዳደሩ ስራውን እንዳይሰራ የጸጥታ ኃይሉን በመያዝ በኃይል እና በሴራ መዋቅሩን እንደበጣጠሱ የሚናገሩ ወገኖች፣ ሹመት ሲሰጣቸው “መንግስት ምን ነካው?” ብለው ነበር።

ከሹመታቸው በኋላ አዲስ አበባ በመመላለስ ለእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን ግብአት ይሆን ዘንድ መድሃኒት፣ በጀት፣ ቀለብ፣ ወዘተ. በትግራይ ሕዝብ ስም በማስፈቀድ ሚሽናቸውን ሲፈጽሙ እንደነበር ዝርዝር መረጃ በማቅረብ የሚከሷቸው ወገኖች፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሹመት ሲረከቡ ስምንት መሰረታዊ ጉዳዮችን እንዲፈጽሙ ወደውና ፈቅደው ፊርማቸውን ቢያኖሩም፣ የፈጸሙት ተቃራኒውን እንደሆነ ያስረዳሉ።

የሹመታቸው ዕለት ዓለም እየሰማ የገቡት ቃል ኪዳን የሚከተሉትን አብይት ጉዳዮች ለማከናወን ነበር፦

  1. በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት በጅምር ያለውን ማጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር ማድረግ።
  2. በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት የትጥቅ መፍታት ሂደቱን ማጠናቀቅ እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋም።
  3. በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ፣ የዜጎችን ደህንነትና መብት ማስከበር።
  4. የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባትና የክልሉን ሁለንተናዊ የልማትና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ማስተባበር።
  5. ከሀገር ሉዓላዊነትና ከሕገ-መንግሥቱ ያፈነገጡ ማናቸውንም ዓይነት ሕገ-ወጥ ግንኙነቶችና እንቅስቃሴዎች በክልሉ እንዳይኖሩ ማድረግ።
  6. ክልሉ ወደ መደበኛ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመለስ የሚያስችል ነፃ፣ ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት ማጠናቀቅ።
  7. የክልሉ ሕዝብ፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ በንቃትና በነፃነት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት።
  8. የክልሉ መንግሥታዊ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ሕዝቦች ትሥሥርና መልካም ግንኙነት የሚያጠናክሩ፣ ሕግና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ።

ታደሰ ወረደ በመጀመሪያው ዓመት የስልጣን ጊዜያቸው አንዱንም ሳይፈጽሙ ጊዜያቸውን አጠናቀቁ። ተጨማሪ ጊዜ በተሰጣቸው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የዶክተር ደብረጽዮንን ቡድን አጨብጭበው ዙፋናቸው ላይ እንዳስቀመጡ በመግለጽ፣ በአውራ አምባ አዘጋጅ ዳዊት ከበደ አማካኝነት “የስልጣን ዘመኔ አላበቃም” የሚል አጀንዳ ማራመድ የጀመሩት፣ የአገር መከላከያና የትግራይ ሰላም ኃይሎች እሳቸውን ጨምሮ አራት ከፍተኛ አመራሮች ከታፈኑበት የኤርትራ ድንበር እንዲለቀቁ ካደረጉ በኋላ መሆኑን በአካሄዳቸው የተበሳጩ ወገኖች አስታውቀዋል።

የአዲስ ሪፖርተር የመቀሌ ተባባሪ ያነጋገራቸው የለውጥ ኃይል አባላት እንዳሉት፣ ታደሰ ወረደ ተመልሶ ስልጣን ስለመያዝ ለማሰብም ሆነ ዘመቻ ለማስጀመር ሞራሉ የላቸውም። ጉዳዩን የትግራይ ሰላም ኃይሎች እና መንግስት በትኩረት እየተከታተሉት እንደሆነ የሚጠቁሙት እነዚሁ ክፍሎች፣ ታደሰ ወረደ በህግ በወንጀል ሊጠየቁ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአውራ አምባ አዘጋጅ አቶ ዳዊት ከበደ በግል እንደ አፈ ቀላጤነታቸው የሚያገለግል መሆኑን የሚናገሩት እነዚህ ወገኖች “አዲስ አበባ ተቀምጦ ማሊያ በመቀያየር በትግራይ ህዝብ ላይ መቆመር፣ ለትግራይ ህዝብ መሪ መምረጥ በዝምታ የሚታለፍ አይደለም” በማለት ማሳሰቢያም አስተላልፈዋል። ከወንጀለኞች ጋር ማበር አብሮ ተጠያቂ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

አቶ ዳዊት ከበደ ለትግራይ የሚዲያ ባለሙያዎችና አክቲቪስቶች ስለ ሚዲያ አሰራር ስልጠና ሲሰጥ “ዳዊት ከአንተ ምን እንማራለን? ከአንተ የምንማረው ከመጣው ጋር መገለባበጥን ነው። አንተ የሚዲያ በጎ ምሳሌ ልትሆን አትችልም” በማለት ተቃውሞና ከፍተኛ ትችት ሲሰነዝሩበት የነበሩ የሚዲያ ባለሙያዎች በበኩላቸው “ዳዊት ለወዲ ወረደ የትግራይን ኮሙኒኬሽን ስራዎች ለመምራት ፕሮጀክት አስገብቶ ጸድቆለት፣ በክፍያ የሚሰራ አገልጋያቸው ነው” በማለት ሰፊ መረጃ አጋርተዋል።

በየጊዜው ታደሰ ወረደን በማቅረብና እሳቸውን ከደሙ ነጹህ የማድረግ ዘመቻ ላይ “ራሱን ሰጥቷል” የሚባለው ዳዊት፣ “ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ቅርብ የሆነው” በሚል ሚዲያዎች ሲጠቅሱት መስማት የተለመደ ነው። አሁንም ከታፈኑበት ከወጡ በኋላ ከዳዊት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ታደሰ ወረደ አዲስ መረጃም እየወጣባቸው ነው።

ታደሰ ወረደ ዳግም ወደ ስልጣን ለመመለስ ዘመቻ መጀመራቸውን ተከትሎ፣ ከዶክተር ደብረጽዮን ከሚመሩት ቡድን ጋር አብረው በመናበብ ይሰሩ እንደነበር፣ አዲስ አበባ የሚመላለሱት ቡድኑ ይዘጋጅበት ለነበረው ጦርነት አስፈላጊ ግብአት ለማሟላት፣ የፌደራል መንግስት ከሚመድበው በጀት እና ቁሳቁስ በቀጥታ የቡድኑን ሰራዊት ይደጉሙ፣ ያደራጁና ልዩ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ያመለከቱት ክፍሎች፤ ታደሰ ወረደ የትግራይ ጊዜያዊ የሽግግር ወቅት እንዲኮላሽ ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በወንጀል መጠየቅ እንዳለባቸው የፌደራል መንግስትን አሳስበዋል።

የቀድሞ ታጋይ ኮሎኔል ገብረዋህድ ለአዲስ ሪፖርተር ሲናገሩ “ወዲ ወረደ ወደ ስልጣን ለመመለስ ማሰቡ አይገርምም። ልክፍት ነው” ካሉ በኋላ “እኔ የምመክረው ያለውን ይዞ በጡረታ እንዲሰናበት ነው። ከዚህ አልፌ እሄዳለሁ ካለ ራሱን ወደ ህግ አቅርቦ ‘ፍረዱብኝ’ እንደማለት ነው። የተከፈላቸው ሚዲያዎችም እንዲህ ካለ ትግራይን እና የትግራይን ህዝብ ለሌላ ስቃይ ከሚዳርግ ሀጢያት ሊቆጠቡ ይገባል” ብለዋል።

ከአሁን በኋላ የትግራይ ህዝብ በራሱ ምርጫ መሪዎቹን መምረጥ እንዳለበት ያመለከቱት ኮሎኔሉ፣ ታደሰ ወረደም ሆነ ሚዲያዎች ይህንን ሀቅ ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም ብለዋል። አክለውም መንግስት በሽግግር ሂደቱ ላይ ከዚህ ቀደም የሰራውን ስህተት እንዳይደግም፣ ሊበጠብጡና የትግራይን ህዝብ ሰላም በድጋሚ ሊቀለብሱ የሚንቀሳቀሱ ማናቸውንም ኃይሎች በትዕግስት ማየት እንደሌለበት አሳስበዋል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related